ህንጻ ቤተክርስቲያን መስራት የሚያሰጠው በረከትና ማድረግ ያለብን ጥንቃቄ

ህንጻ ቤተክርስቲያን መስራት የሚያሰጠው በረከትና ማድረግ ያለብን ጥንቃቄ

ዲ/ን ኅሩይ ውቤ

እግዚአብሔር አምላካችን ሰማይ ዙፋኑ፣ ምርድም የእግሩ መረገጫ ነውና በጊዜና በቦታ አይወሰንም፡፡ ይህ መወሰንና መመርመር የሌለበት አምላካችን ምንጊዜም ፈቃዱን ለሚያደርጉ ሰዎች ቅርብ ነው፡፡ እግዚአብሔር ለሚያምኑበት ቅርብ መሆኑን ከገለጠባቸው መንገዶች አንዱ ደግሞ ምዕመናን በስሙ ተሰብስበው በቤተ መቅደስ ሲጸልዩ ጸሎታቸውን እንደሚሰማ፣ ልመናቸውን እንደሚፈጽም የገባው ዘላለማዊ ቃልኪዳን ነው፡፡ በ2ኛ ዜና መዋዕል 7፡15-16 “አሁንም በዚህ ስፍራ ለሚጸለይ ጸሎት ዐይኖቼ ይገለጣሉ፤ ጆሮቼም ያዳምጣሉ፡፡ አሁንም ስሜ ለዘላለም በዚያ ይኖር ዘንድ ይህን ቤት መርጫለሁ፤ ቀድሻለሁም፤ ዐይኖቼና ልቤም ዘወትር በዚያ ይሆናሉ” ብሏልና፡፡

በብዙ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት አዲስ ሕንፃ ቤተክርስቲያን መስራትና ያረጀውን ማደስ በተደጋጋሚ የሚደረግ መንፈሳዊ ዋጋው ከፍ ያለ የጽድቅ አገልግሎት ነው፡፡ ለዚህም ሰበካ ጉባኤ ሕንጻ አሰሪ ኮሚቴዎች በየቦታው ምዕመናንን በማስተባበር ለመንፈሳዊ ሥራ እንደሚያተጉ ይታወቃል፡፡ ይህን ለማድረግም በቃለ እግዚአብሔር መሰረትነት የታነጸ መንፈሳዊ ግንዛቤ እጅግ በጣም ወሳኝ ነው፡፡ ለዚህም እንዲረዳን ሕንፃ ቤተክርስቲያን ለምን፣ እንዴትና በምን ሁኔታ መሰራት እንዳለበት ከቅዱሳት መፃሕፍት በማጣቀስ ምዕመናንና ምዕመናትን መልካም ለሆነ መንፈሳዊ ፍሬ ለማነቃቃት ይህችን አጭር እናንብባት፡፡

  • ቤተ መቅደስን ለመስራት መመረጥ መታደል ነው

ቤተ መቅደስ የእግዚአብሔር ማደሪያ ነው፡፡ እግዚአብሔር የሚያድርበትን ቤት ለመስራት መታደል ደግሞ የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ ነው፡፡ በቅዱስ መጽሐፍ ታሪኩ እንደተቀመጠው ነቢየ እግዚአብሔር ንጉስ ዳዊት የእግዚአብሔር ማደሪያ ቤተመቅደስን ሳይሰራ እረፍት እንደማያገኝ በተናገረበት መዝሙሩ እንዲህ ብሎ ነበር፡- “ወደ ቤቴ ድንኳን አልገባም፣ ወደ መኝታዬም አልጋ አልወጣም፣ ለዐይኖቼም መኝታን፣ ለቅንድቦቼም እንቅልፍን፣ ለጉንጮቼም ዕረፍትን አልሰጥም፣ የእግዚአብሔርን ቦታ፣ የያዕቆብ አምላክን ማደሪያ እስካገኝ ድረስ” መዝ. 131፡3-5 ይህንን መልካም ምኞቱን የተረዳ ነቢዩ ናታንም የንጉስ ዳዊትን የእግዚአብሔርን ማደሪያ ለመስራት መነሳሳት አስተውሎ ፈቃደ እግዚአብሔርን ለማወቅ ሱባኤ ገብተዋል፡፡ በ1ኛ ዜና መዋዕል 17፡1-27 ካለው የቅዱስ መጽሐፍ ንባብና በመንፈስ ቅዱስ የተመሩ አባቶቻችን ካስተማሩን ታሪክ እንደምንረዳው ምንም እንኳ ንጉስ ዳዊት እጅግ በርካታ መንፈሳዊ ስራ በመስራት እግዚአብሔርን ያስደሰተ ቢሆንም ጌታ ግን ንጉስ ዳዊት በድካሙ ወራት የሰራውን ኃጢአት አስቦ እንዲጸጸት ቤተ መቅደስ ለመስራት እርሱ እንዳልተመረጠ ነገረው፡፡ ይሁንና የዳዊትን ቅንነት ተመልክቶ ልጁ ሰሎሞን ቤተመቅደስን እንዲሰራ የእግዚአብሔር ፈቃዱ ሆነ፡፡ ከዚህ የምንረዳው ነገር ቢኖር ቤተ መቅደስን ለመስራት መመረጥ እንደ ሰው ሀሳብ ብቻ ሳይሆን እንደ እግዚአብሔር ቅዱስ ፈቃድ የሚደረግ መሆኑን ነው፡፡ የንጉስ ዳዊትን ኃጢአት አስቦ ቤተ መቅደስን ከመስራት የሚገድብ ቀኖና የሰጠው አምላካችን እግዚአብሔር እኛን ምዕመናንን ቤቱን እንድንሰራ ሲፈቅድልን እንደ ንጉስ ዳዊት “አቤቱ አምላክ ሆይ ለዘላለም የወደድከን፣ እንደ ባለ ማዕረግ ሰው የተመለከትኽን እኛ ማን ነን?” ብለን ልናመሰግነው ይገባል፡፡ ጌታ በደለኞች ስንሆን ይህን በረከት ለእኛ ሲሰጠን “ኀጢአታቸው የተተወላቸው፣ በደላቸውንም ሁሉ ያልቆጠረባቸው ብፁዓን ናቸው” ተብሎ በመዝሙረ ዳዊት 31፡1 የተጠቀሰው የእግዚአብሔር ቃል እውነትነት ስለተገለጠ በደላችንን አይቶ ከዚህ የበረከት አገልግሎት ያልከለከለንን አምላካችንን ልናመሰግነው ይገባል፡፡ ቤተመቅደስን ለመስራት በመመረጣችን ልንደሰትና ቅን አገልግሎትን ልንፈጽም ያስፈልጋል፡፡

  • ምዕመናን ሁላችንም እንደአቅማችን የመሳተፍ ግዴታ አለብን

በቅዱሳት መፃሕፍት ከተቀመጡ መለኮታዊ ትዕዛዛት አንዱ አምላካችንን በፍጹም ልባችን በፍፁም ኃይላችን መውደድ ነው፡፡ እግዚአብሔርን መውደድ ማለት ሀሳባዊ ብቻ ሳይሆን በተግባር የሚገለጥ መሆን አለበት፡፡ በርካታ ቅዱሳን ለእግዚአብሔር ያላቸውን ፍቅር ስሙ የሚመሰገንበት ቤተ መቅደስ በመስራት ገልጸዋል፡፡ እኛም ይህን የማድረግ መንፈሳዊ ግዴታ አለብን፡፡ እስራኤላውያን በምርኮ በነበሩበት ዘመን ቤተ መቅደስን ከመስራት ቸል ባሉ ጊዜ የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ብሎ ወቅሷቸው ነበር፡- “በውኑ ይህ ቤት ፈርሶ ሳለ እናንተ ራሳችሁ በተሸለሙ ቤቶቻችሁ ለመኖር ጊዜው ነውን?” ትንቢተ ሐጌ 1፡4፡፡ ይህ የእግዚአብሔር ቃል እኛንም ይገስጸናል፡፡ ስለሆነም እኛ ባማሩ ቤቶች እየኖርን የእግዚአብሔርን ማደሪያ ከመስራት ቸል ልንል አይገባንም፡፡ ብዙዎቻችን የሰበሰብነውን ገንዘብ የሰጠን አምላካችን መሆኑን ዘንግተን ለመንፈሳዊ አገልግሎት ገንዘብ መስጠትን አክብደን እናየዋለን፡፡ እንደእኛ ለመንፈሳዊ አገልግሎት ንፉግ የነበሩትን እስራኤላውያን የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ብሎ ወቅሷቸው ነበር፡- “እስኪ መንገዳችሁን አስቡ፡፡ ብዙ ዘራችሁ፤ ጥቂትም አገባችሁ፤ በላችሁ፤ ነገር ግን አልጠገባችሁም፤ ጠጣችሁ፤ ነገር ግን አልረካችሁም፤ ለበሳችሁ፤ ነገር ግን አልሞቃችሁም፤ ደመወዙን የተቀበለም በቀዳዳ ከረጢት ሰበሰበ፡፡” ትንቢተ ሐጌ 1፡6፡፡ ያጡትን በረከት እንዲያገኙም እግዚአብሔር እንዲህ አላቸው “በልባችሁ መንገዳችሁን አስቡ፡፡ ወደ ተራራው ውጡ፤ እንጨትንም ቁረጡ፤ ቤቱንም ስሩ፤ እኔም በእርሱ ደስ ይለኛል፤ እመሰገናለሁም፡፡” ትንቢተ ሐጌ 1፡7-8፡፡ ለእግዚአብሔር ቃል የታዘዙ እስራኤል ዘስጋ በዘሩባቤል ተመርተው የአምላካቸውን የእግዚአብሔርን ቤት መስራት ጀመሩ፡፡ እኛም የቅዱሳን በረከት እንዲደርሰን በሕንፃ ቤተክርስቲያን ግንባታው በአቅማችን የመሳተፍ ግዴታችንን መወጣት እንዳለብን የእግዚአብሔር ቃል ይመክረናል፣ ያስተምረናል፡፡

  • የሰይጣንን ፈተና በድል ለመወጣት መዘጋጀት አለብን

ማንኛውም መንፈሳዊ አገልግሎት የበጎ ነገር ጠላት ከሆነ ከዲያብሎስ የሚነሳ ፈተና አያጣውም፡፡ ለዚያ ነው አባቶቻችን “ያለ መከራ ጸጋ አይገኝም” በማለት የሚያስተምሩን፡፡ ሕንፃ ቤተክርስቲያን ለመስራት ስንነሳ በብዙ መልኩ የሚመጣ የሰይጣን ፈተና እንደሚኖር ተገንዝበን ራሳችንን በመንፈሳዊ ኃይልና ጥበብ ማዘጋጀት፣ እግዚአብሔርንም መማጸን አለብን፡፡ ከፈተናዎች የመጀመሪያ ሊሆን የሚችለው የተስፋ መቁረጥ ፈተና ነው፡፡ ስራው ረጅምና ከባድ በሆነ ቁጥር ተስፋ የሚቆርጥ ሰው ሊበዛ ይችላል፡፡ ነቢየ እግዚአብሔር ነህምያ የኢየሩሳሌምን የፈረሱ ቅጥሮች፣ የተቃጠሉ በሮች ጉዳይ ሰምቶ በፆምና በጸሎት እግዚአብሔርን እየለመነ ወገኖቹን እስራኤላውያንን “አሁንም ከእንግዲህ ወዲህ መሳለቂያ እንዳንሆን የኢየሩሳሌምን ቅጥር እንሥራ” ባላቸው ጊዜ ለበጎ ሥራ እጆቻቸውን ያበረቱ እንደነበሩ ሁሉ በሚሰሩት ላይ በንቀት የሚስቁባቸውም እንደነበሩ መጽሐፍ ቅዱስ ያስተምረናል፡፡ በንቀት በሚስቁት ሰዎች ያልተሸነፈው ነቢየ እግዚአብሔር ነህምያም “የሰማይ አምላክ ያከናውንልናል፤ እኛም ንጹሓን ባሪያዎቹ ተነስተን እንሰራለን” መጽ. ነህ. 2፡20 በማለት እግዚአብሔርን አጋዥ በማድረግ የሰይጣንን ፈተና በድል ለመወጣት እንደምንችል አብነት የሚሆን ታሪክ ሰርቶ አልፏል፡፡ እኛም አዲሱን ሕንፃ ቤተክርስቲያናችንን ስንሰራ እግዚአብሔርን ተስፋ በማድረግ በመንፈሳዊ ኃይልና ብርታት ልንነሳ ይገባል፡፡

 

  • የጽድቅ አገልግሎታችን በአሰራር ችግር መንፈሳዊነቱን እንዳያጣ መጠንቀቅ አለብን

ሕንፃ ቤተክርስቲያንን መስራት የተቀደሰ ስራ ስለሆነ የተቀደሰ አሰራር ይፈልጋል፡፡ የጽድቅ አገልግሎት መንፈሳዊ በሆነ አመራር መደገፍ አለበት፡፡ በአንዳንድ ቦታዎች ሕንፃ ቤተክርስቲያን ለመስራት የሚሆን ገንዘብ ለመሰብሰብ መንፈሳዊ አሰራርን የሚቃረን አካሄድ እንደሚደረግ ይታወቃል፡፡ ሕንፃ ቤተክርስቲያን ለመስራት የሚውል ገንዘብ ለመሰብሰብ ከመንፈሳዊ አሰራር መራቅ የለብንም፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “የአባቴን ቤት የንግድ ቤት አታድርጉ” ዮሐ. 2፡16 በማለት አይሁድን የወቀሳቸው ተመሳሳይ ስራ እየሰሩ እግዚአብሔርን ስላሳዘኑ ነበር፡፡ ስለሆነም እኛ ሕንፃ ቤተክርስቲያን ለመስራት በምናደርገው ጥረት ከሕንፃ ቤተክርስቲያን በላይ የከበረ የእግዚአብሔርን ቃል የሚቃረን አሰራር እንዳንከተል አካሄዳችንን በጥንቃቄ መመርመር ይጠበቅብናል፡፡ ቃሉን ስንጠብቅ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ይሆናል፡፡ “እግዚአብሔር ቤትን ካልሰራ ቤትን የሚሰሩ በከንቱ ይደክማሉ” መዝ. 126፡1 እንደተባለ ከቃለ እግዚአብሔር ጋር የሚጣላ አሰራር ከተከተልን ግን ድካማችን ዋጋ የሌለው ይሆንብናል፡፡

  • ሕንፃ ቤተክርስቲያን ለሰው ይሰራል እንጂ ሰው ስለ ሕንፃ ቤተክርስቲያን አልተፈጠረም

ብዙ ቦታዎች ላይ በተደጋጋሚ ከሚስተዋሉ ችግሮች ውስጥ አንዱ ሕንፃ ቤተክርስቲያንን ለመስራት በሚል ሰበብ መንፈሳዊ አገልግሎትን ቁሳዊ ማድረግና የቤተክርስቲያንን ዋነኛ ተልዕኮ መዘንጋት ነው፡፡ ሕንፃ ቤተክርስቲያንን መስራት ክብር የሚሆነው ሕንፃ ሥላሴን (ምዕመናንና ምዕመናትን) በእምነትና በምግባር ለማሳደግ ስንጠቀምበት ብቻ ነው፡፡ ቤተክርስቲያን ዋና ተልዕኮዋን ዘንግታ ፎቅና ሕንፃ በማሳመር ብቻ መጠመድ የለባትም፡፡ ሕንፃ ቤተክርስቲያን ለሰው ይሰራል እንጂ ሰው ስለ ሕንፃ ቤተክርስቲያን አልተፈጠረምና፡፡ ስለሆነም ለሕንጻ ቤተክርስቲያን ገንዘብ ለማሰባሰብ ሲባል የእግዚአብሔርን ቅዱስ ቃል በቃሉ ለሚነግዱ ምንደኞች፣ ለፖለቲከኞች፣ ለዘረኞችና ለእወደድ ባይ “አገልጋዮች” ዓላማ መሸቀጥን ልንከላከል ይገባል፡፡ ቃሉን ጠብቀን ስናገለግል እግዚአብሔር የሰማያዊት ኢየሩሳሌም አምሳል የሆነች ሕንፃ ቤተክርስቲያንን በእኛ አድሮ ይሰራል፡፡ በቁሳዊ እይታ ተጠምደን ቃሉን ችላ ስንል ግን እግዚአብሔር ከእኛ ይለያል፡፡ እግዚአብሔር የሌለበት ሕንፃ ደግሞ ቁሳዊ እንጂ መንፈሳዊ ዋጋ የለውም፡፡ የተወደደ ሐዋርያ ቅዱስ ዮሐንስ እንዳስተማረን “ፍጹም ዋጋ እንድታገኙ እንጂ የሠራችሁትን እንዳታጡ ራሳችሁን እወቁ፡፡” (2ዮሐ. 1፡8) ተብለናልና በምናደርገው መንፈሳዊ አገልግሎት ፍጹም ዋጋ ለማግኘት እንድንችል የሠራነውን ከሚያሳጡ፣ ከመንፈሳዊ አሰራር ከሚያወጡ አካሄዶች ርቀን በፍጹም መንፈሳዊ ፍቅርና መታዘዝ የሰማያዊት ኢየሩሳሌም አምሳል የሆነች ሕንፃ ቤተክርስቲያንን ለመስራት ልንፋጠን ይገባል፡፡ በዚህም የቅዱሳንን በረከት እንካፈላለን፡፡

አምላካችን እግዚአብሔር በመንፈሳዊ ኃይል አነሳስቶ ሕንፃ ቤተክርስቲያናችንን ሰርተን ለመፈጸም ያብቃን፡፡ ለዚህም የእመቤታችን አማላጅነት፣ የሊቀ መላዕክት ቅዱስ ሚካኤል ተራዳኢነት አይለየን፡፡