ሆሣዕና

ሆሣዕና

በመጋቤ ሐዲስ ፍቅረ ማርያም ባዘዘው

በቦሌ መንበረ ብርሃን ቅዱስ እግዚአብሔር አብ ቤተክርስቲያን የሐዲስ ኪዳን የትርጓሜ መምህር

 

ፍትሕዎን ወአምጽእዎን ሊተ

ፈትታችሁ አምጡልኝ ማቴ.21፤2

ዐቢይ ጾም ከገባ ይህ ስምንተኛ ሳምንት ሲሆን ዕለቱም ሆሳዕና ተብሎ ይጠራል፡፡ ይህም ሲባል የዓለም መድኃኒት መሆኑን ወይንም ሰውን ለማዳን ሰው የሆነበት ሰማያዊ ምሥጢር የሚነገርበት ቀን ነው፡፡ ቅዱስ ወንጌል እንዲህ ይላል፡- ወደ ኢየሩሳሌምም ቀርበው ወደ ደብረ ዘይት ወደ ቤተ ፋጌ ሲደርሱ፥ ያንጊዜ ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ሁለት ላከ፥ እንዲህም አላቸው፦ በፊታችሁ ወዳለችው መንደር ሂዱ፥ በዚያን ጊዜም የታሰረችን አህያ ውርንጫም ከእርስዋ ጋር ታገኛላችሁ፤ ፈትታችሁ አምጡልኝ። ማንም አንዳች ቢላችሁ። ለጌታ ያስፈልጉታል በሉ፤ ወዲያውም ይሰዳቸዋል። ለጽዮን ልጅ። እነሆ፥ ንጉሥሽ የዋህ ሆኖ በአህያ ላይና በአህያይቱ ግልገል በውርንጫይቱ ላይ ተቀምጦ ወደ አንቺ ይመጣል በሉአት ተብሎ በነቢይ የተነገረው ይፈጸም ዘንድ ይህ ሆነ። ደቀ መዛሙርቱም ሄደው ኢየሱስ እንዳዘዛቸው አደረጉ፥ አህያይቱንና ውርንጫዋንም አመጡለት፥ ልብሳቸውንም በእነርሱ ላይ ጫኑ፥ ተቀመጠባቸውም።

እንደሚታወቀው አካላዊ ቃል ሰው የሆነበት ምሥጢር በመከራ ውስጥ የነበረውን የሰው ዘር በሙሉ በሞቱ ሞትን ድል ነሥቶ ከባርነት ቀንበር ነጻ ለማውጣት ነበር፡፡ የሰው ልጅ ከእግዚአብሔር ሕግ ይልቅ ለራሱ የፈቃድ ሕግ የተገዛ በሞት ጥላ ውስጥ ሲርመሰመስ የነበረ፤ የብርሃንን ጮራ በተስፋ የሚጠባበቅ ከመከራው የተነሣም ሁለንተናው በኃጢአት የጠቆረ ሆኖ እንዲህ የሚልን ድምጽ ሲያሰማ የነበረበት ወቅት ነበር፡፡ ኢትርአያኒ እስመ አነ ጸላም እስመ ኢርአየኒ ፀሐይ መሐልይ.1፤6 ጥቁር ነኝና አትዩኝ ፀሐይ አላየኝምና፡፡ ይህ የሚገልጸው ሰዎች እንዴት ባለ የመከራ ሕይወት ውስጥ ማለፋቸውንና ከመከራው ጽናት የተነሣ ጥቁር ነን አትዩን መከራው አጥቁሮናል የእኛ መልክ የሚያምረው ውብ የሚሆነው ፀሐይ ሲወጣ ነው አሁን ጊዜው ጨለማ ነው ፀሐይ አልወጣም በማለት ክርስቶስ ፀሐየ ጽድቅ እርሱ ሰው እስኪሆን በተስፋ ደጅ ይጸኑ ነበር፡፡ ፀሐይ ኢየሱስ ክርስቶስ ከምሥራቅ ድንግል ማርያም እስኪወጣ በተስፋ ሲማጸኑ ኑረዋል፡፡ ጊዜው ሲደርስ ኢየሱስ ክርስቶስ ከድንግል ማርያም ተወለደ፡፡ በነፍሱም በሥጋውም በኃጢአት የታሰረውን ሰው ይፈታው ዘንድ ሁለቱን ደቀ መዛሙርት ወደ ታሰሩት ላከ፡፡ የሚገርመው ነገር ደግሞ የታሰሩት ሁለት ናቸው የተላኩትም ሁለት ናቸው፡፡ ሁለቱ በእስራት ውስጥ የነበሩት ነፍስና ሥጋ ናቸውና፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስም ክድንግል ማርያም የነሣው ሁለቱን ነፍስና ሥጋን ነው ለምን ሲባል ሁለቱም ድኅነት ይፈልጉ ነበርና፡፡ ነፍስና ሥጋን አልነሣም ከተባለ ግን አዳም በነፍሱም በሥጋውም አልዳነም ማለት ነው፡፡

ሁለቱ አዳምና ሔዋን እንዲሁም ሁለቱ ነፍሥና ሥጋ ከታሰሩበት ዓለም ከተባለ መንደር ሁለቱ knowledge and wisdom ( እውቀትና ጥበብ) የተባሉ ደቀ መዛሙርት የታሠሩትን  ፈትተው ያመጡ ዘንድ ተላኩ የሚገርመው ነገር የሚከራከራችሁ ቢኖር ለጌታ ያስፈልጉታል ወይንም ጌታቸው ይፈልጋቸዋል በሉ አላቸው፡፡ በነፍስም በሥጋም አክብሮ የፈጠረን እርሱ ነውና ደስ የሚለው እርሱ ሁሌም ቢሆን በኃጢኣት እስራት ውስጥ ያሉትን ሰዎች መፈለጉ ነው፡፡ አዳምና ሔዋን  ከገነት የወጡት ሁለቱን ነገር እውቀትንና ጥበብን በማጣታቸው ነበር፡፡ ይህ ሲባል ግን እግዚአብሔር የሰጣቸውን እርሱን የሚያውቁበትን እውቀት ሰይጣን በሽንገላ ስለወሰደባቸው ነው፡፡ እግዚአብሔር ምን እንዳላቸው ያውቃሉ እርሱ ካላቸው ይልቅ ግን የሰይጣንን ተልኮልና ሽንገላ ሰሙ፡፡ በመሆኑም እነርሱ ፍጡራን እግዚአብሔር ፈጣሪ እንደሆነ  የሚያውቁበት እውቀት ከእነርሱ በሸንገላ ሲወሰድ ያኔ ከበለስ ሥር ክብራቸውን አጡ፡፡ ለዚህም ነበር ሁለቱ በአዳም ውስጥ የነበሩት ነገር ግን የጠፉበት እውቀትና ጥበብ ወደታሰሩት ሰዎች የተላኩ፡፡ እነኝህ እውቀትና ጥበብ ለእግዚአብሐር እንድንገዛ የሚያደርጉ ናቸው፡፡ ዕውቀትም ጥበብም እግዚአብሔርን መፍራት ስለሆኑ ነው፡፡ አንድ ሰው እውቀት አለው ተብሎ እንዲሁም ጥበበኛ ነው ተበሎ ለእግዚአብሔር እንደ እግዚአብሔርነቱ ካልተገዛ እውቀቱም ሆነ ጥበቡ ብላሽ ነው፡፡ እግዚአብሔር ለሁሉም ሰው ከሆነ፤ በመስቀል ላይ ከተሰቀለ፤ ሁለቱ ደቀ መዛሙርት እንዲሁ ወደዓለም ከተላኩ ዛሬም ይህ ተዘንግቶ በዘር፤ በጎሳ የሚለያይ ከሆነ የዚህ ሰው እውቀት እንዲሁም ጥበብ እውቀትና ጥበብ መባሉ ቀርቶ ድንቁርናና ብልሹነት ቢባል ይቀላል፡፡ ወደ እግዚአብሔር የሚያደርስ እውቀትም ይሁን ጥበብ የለውምና፡፡ እግዚአብሔርን የምናውቅበት እውቀትና ጥበብ ለቅድስና፤ ለትህትና ያበቃልና ከዚያም ለእርሱ ማደሪያ ወደ መሆን ያደርሳል፡፡ በዛሬውም ወንጌል የምንመለከተው ይህን ነው፡፡ ሁለቱ ደቀ መዛሙርት የተባሉት እውቀትና ጥበብ ወደ ዓለም ሲገቡ ሁሉም ሰው ራሱን ለእግዚአብሔር ማደሪያነት ዝግጁ ያደርጋል፡፡ ሁለቱ የታሰሩት አህያና ውርንጫይቱ ሁለቱ ደቀ መዛሙርቱ ተልከው ካስፈቷቸው በኋላ ልብስ አለበሷቸው ከዚያም ለጌታቸው መቀመጫነት ብቁ ሆኑ፡፡ በጥበብና በእውቀት የተገነባ ሰው ልብስ ለተባለው ቅድስና ሕይወት ብቁ ይሆናል፡- ራእይ፣7፤9 ከዚህ በኋላ አየሁ፥ እነሆም፥ አንድ እንኳ ሊቆጥራቸው የማይችል ከሕዝብና ከነገድ ከወገንም ከቋንቋም ሁሉ እጅግ ብዙ ሰዎች ነበሩ፤ ነጭ ልብስም ለብሰው የዘንባባንም ዝንጣፊዎች በእጆቻቸው ይዘው በዙፋኑና በበጉ ፊት ቆሙ፤ በታላቅም ድምፅ እየጮሁ። በዙፋኑ ላይ ለተቀመጠው ለአምላካችንና ለበጉ ማዳን ነው አሉ መላእክቱም ሁሉ በዙፋኑና በሽማግሌዎቹ በአራቱም እንስሶቹ ዙሪያ ቆመው ነበር፤ በዙፋኑም ፊት በግምባራቸው ተደፉ፥ ለእግዚአብሔርም እየሰገዱ። አሜን፥ በረከትና ክብር ጥበብም ምስጋናም ውዳሴም ኃይልም ብርታትም ከዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ ለአምላካችን ይሁን፤ አሜን አሉ። ከሽማግሌዎቹም አንዱ ተመልሶ፦ እነዚህ ነጩን ልብስ የለበሱ እነማን ናቸው? ከወዴትስ መጡ? አለኝ። እኔም። ጌታ ሆይ፥ አንተ ታውቃለህ አልሁት። አለኝም። እነዚህ ከታላቁ መከራ የመጡ ናቸው፥ ልብሳቸውንም አጥበው በበጉ ደም አነጹ። ስለዚህ በእግዚአብሔር ዙፋን ፊት አሉ፥ ሌሊትና ቀንም በመቅደሱ ያመልኩታል፥ በዙፋኑም ላይ የተቀመጠው በእነርሱ ላይ ያድርባቸዋል። እንዲህ ባለ ሕይወት ሰው ብቁ ሲሆን ያኔ እግዚአብሔር በእርሱ ላይ ለማደር ይፈልጋል፡፡ ምክንያቱም የቅድስናን ልብስ ተጎናጽፏልና፡፡ ከዚህ በኋላም እግዚአብሔር ባከበረው ሕይወት ውስጥ የሚነጠፈው የክብር ምንጣፍ ብዙ ነው ያውም ሞት ሊይዘው የማይችል፡፡ ቅዱሳን ዛሬም የምናከብራቸው በሚያልፈው ዓለም ውስጥ የማያልፍ ሥራ ሰርተው ስላለፉ ነው፡፡ በአጠቃላይ ልብሶቹ እውነት፤ ቅድስና፤ትዕግሥት፤ ሃይማኖት ናቸው፡፡ እነኚህ ሁሉ ካሉ እግዚአብሔር ሁሌም ከእኛ ሕይወት ውስጥ ይኖራል፡፡

ይቆየን

ገብር ኄር

ገብር ኄር 

በመጋቤ ሐዲስ ፍቅረ ማርያም ባዘዘው

በቦሌ መንበረ ብርሃን ቅዱስ እግዚአብሔር አብ ቤተክርስቲያን የሐዲስ ኪዳን የትርጓሜ መምህር

 

እንደሚታወቀው የዐቢይ ጾም ስድስተኛ ሳምንት ገብር ኄር በመባል ይታወቃል፡፡ ለመሆኑ ገብር ኄር ሲባል ምን ማለት ነው? ገብር ኄር ሲባል ታማኝ አገልጋይ ማለት ሲሆን ታመኝነቱም ለራሱና ለፈጣሪው ነው፡፡ ስለዚህ ለዛሬው ርእስ የምናደርገው ታማኝነት በሚል ነው፡፡

ታማኝነት 25፤21

ቅዱስ ቃሉ እንዲህ ይላል፡- ማቴ.25፤14-23 ወደ ሌላ አገር የሚሄድ ሰው ባሮቹን ጠርቶ ያለውን ገንዘብ እንደ ሰጣቸው እንዲሁ ይሆናልና፤ ለእያንዳንዱ እንደ ዓቅሙ፥ ለአንዱ አምስት መክሊት ለአንዱ ሁለት ለአንዱም አንድ ሰጠና ወደ ሌላ አገር ወዲያው ሄደ። አምስት መክሊትም የተቀበለው ሄዶ ነገደበት ሌላም አምስት አተረፈ፤ እንዲሁም ሁለት የተቀበለው ሌላ ሁለት አተረፈ። አንድ የተቀበለው ግን ሄዶ ምድርን ቈፈረና የጌታውን ገንዘብ ቀበረ። ከብዙ ዘመንም በኋላ የእነዚያ ባሮች ጌታ መጣና ተቆጣጠራቸው። አምስት መክሊት የተቀበለውም ቀረበና ሌላ አምስት መክሊት አስረክቦ። ጌታ ሆይ፥ አምስት መክሊት ሰጥተኸኝ ነበር፤ እነሆ፥ ሌላ አምስት መክሊት አተረፍሁበት አለ። ጌታውም። መልካም፥ አንተ በጎ ታማኝም ባሪያ፤ በጥቂቱ ታምነሃል፥ በብዙ እሾምሃለሁ፤ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ አለው። ሁለት መክሊትም የተቀበለው ደግሞ ቀርቦ። ጌታ ሆይ፥ ሁለት መክሊት ሰጥተኸኝ ነበር፤ እነሆ፥ ሌላ ሁለት መክሊት አተረፍሁበት አለ። ጌታውም። መልካም፥ አንተ በጎ፥ ታማኝም ባሪያ፤ በጥቂቱ ታምነሃል፥ በብዙ እሾምሃለሁ፥ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ አለው። በአንጻሩም ደግሞ የተቀበለውን ቀብሮ ያኖረ በመጨረሻም የተፈረደበት ሰው አለ፡፡

እኛ ማየት የሚገባን ሠርቶ ያተረፈውን ነው፡፡ ብዙ ጊዜ የሰው ልጆች ሰርተው ያተረፉትን ሳይሆን የተቀበሉትን ሳያተርፉ የቀሩትን ሰዎች አብነት ሲያደርጉ ይስተዋላሉ፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ ግን የሠሩትን ወይንም ያተረፉትን የምንመለከት ከሆነ ለተቀበልነው ዓላማ ብቁዎች እንሆን ነበር፡፡ እንግዲህ በዚህ ምዕራፍ ውስጥ የምንመለከተው አንድ ቁም ነገር አለ፡፡ እርሱም ታማኝ መሆንን ነው፡፡ ታማኝነት ለራስም ለወንድምም ለፈጣሪም እንዲሁም ለአገርም ይጠቅማል፡፡ ወንጌሉ እምደሚነግረን አንድ ባዕለ ጸጋ ለሦስት ሰዎች ለእያንዳንዳቸው እንደየአቅማቸው ለእንደኛው አምስት፤ ለሁለተኛው ሁለት፤ ለሦስተኛው አንድ መክሊት ወይንም ገንዘብ ሰጣቸው፡፡ የተቀበሉትም እንዲሠሩበት ነበር፡፡ ባለ አምስቱና ባለሁለቱ አትርፈው ሲመሰገኑ ባለ አንዱ ግን የተቀበለውን ነገር መሬት ውስጥ ቆፍሮ አስቀመጠው፡፡ እንደሚታወቀው እግዚአብሔር አባታችን ለእኛ ሁሉን ነገር አድርጓል ያጎደለብን ነገር የለም፡፡ ለአንዱ አንድ መክሊት መስጠቱ እርሱ ሁላችን አንድ የአዳም ዘሮች መሆናችንን ያጠይቃል ሁለት መስጠቱ ደግሞ በእኛ ውስጥ ፍቅረ ቢጽና ፍቅረ እግዚአብሔር መኖሩን ያጠይቃል አምስት መስጠቱ ደግሞ በእኛ ውስጥ ያሉ አምስት የስሜት ዕዋሳትን ያጠይቃሉ ማለት ነው፡፡

እንግዲህ ነገሩ እንዲህ ከሆነ ባለ ዕዳዎቹ እኛው ነን ማለት ነው ሁሉም ሰው ሁሉን ተቀብሏል ግን ሁሉም አትራፊ ሳይሆን አጉዳይ ሆኗል፡፡ ባለ አንዱን እንውሰድ የሰው ልጀች አንድ የአዳም ዘሮች መሆናችን በዚህ ወቅትና በዚህ ሰዓት የተረሳ ወይንም የተካደ በሚመስል ሁኔታ ሰው ሁሉ ከእግዚአብሔር አንድነት ፍቅር ወጥቷል አንዱ አንዱን ገፍቶ ሁሉም ነገር የእኔ የሚል አባዜ በውስጡ ነግሧል፡፡ ስለአንድነት ከመስበክ ይልቅ ስለመለያት የሚሰብከው በዝቷል፤ አንድነትን የሚሰብከው ኢትዮጵያዊነት ውስጣችን ጠፍቷል በአጠቃላይ በሚባል ሁኔታ የሰዎች እይታ ከፈጣሪ እይታ ውጭ ሆኗል ምክንያቱም ሁላችን አንድ አባት ካለን እኛ ሁላችንም አንድ ነን እንጅ ሁለት አይደለንም ምን አልባትም ሁለት ነን ብለው የሚያስቡት ከአንድ አባት ውጭ የተወለዱ ሲሆኑ ብቻ ነው፡፡

የእግዚአብሔር ልጆች በአንድ መንፈስ፤ በአንድ ኃይል፤ በአንድ ዕውነት ሥር ያደጉ ናቸውና ሕይወታቸውም እንዲሁ ነው፡፡ በዚህ ዓለም ውስጥ ሲኖሩ ራሳቸውን በእግዚአብሔር የህግ ጥላ ሥር የሚያስጠልሉ፤ ዋሽተው ቀምተው ከመኖር ይልቅ በአንድ በዕውነት መንገድ ውስጥ ኖረው ለመንግሥቱ የተዘጋጁ፤ በንግግር ሱስ የተጠመዱ ሳይሆኑ ዕውነቱን ዕውነት ሐሰቱን ሐሰት በሚለው ዕውነተኛ ወንጌል ውስጥ በቅለው ያደጉ፤ ከመለያየት መንፈስ ይልቅ የአንድነትና የፍቅር መንፈስ ውስጣቸውን ያበለጸጋቸው፤ ከዚህ ዓለም ውጭ ዕውነተኛው ዓለም እንዳለ የተገነዘቡ፡፡ ከጊዜያዊ ጥቅም ይልቅ ዘለዓለማዊውን የእግዚአብሔርን መንግሥት የሚያስቡ፤ የአንድ አባት ያውም የእግዚአብሔር ልጆች እንደመሆናቸው መጠን በእርሱ ፍቅር ውስጥ የሚኖሩ እኒህ ናቸው የእንድነትን መክሊት ከፈጣሪያቸው አስቀድሞ በተፈጥሮ ከዚያም በሞቱ ተቀብለው  በምድራዊ ሀሳብ ማንነት ሰማያዊውን መክሊት ሳይቀብሩ ሰማያዊ ሀብት እንደመሆኑ መጠን በአንድ ፍቅር ጠብቀው ያስጠበቁ ዕውነተኞች ክርስቲያኖች እነኝህ ናቸው፡፡ በአንጻሩም የአንድነት ፍቅር ያልገባቸው በተፈጥሮና እና እንዲሁ የሞት ዋጋ የተከፈለበትን ማንነት ተቀብለውት ነገር ግን ለተቀበሉት ነገር ብቁ ሳይሆኑ ቀብረው ያስቀሩ የፈጣሪያቸውን ማንነት የዘነጉ ናቸውና ጥያቄው አይቀርም በተፈጥሮና በሞት ውስጥ አልፌ የሰጠውህን ማንነቴን አምጣ ወይንም የት ጣልከው ሲባል መልስ ማጣት ይከብዳል፡፡ ሌላ ነገር ሳይሆን የተቀበሉትን ነገር ለተቀበሉለት ዓላማ ብቁ ማድረግ አለመቻል ያስጠይቃልና ነው፡፡

በዚህ የበሽታ አባዜ ሁሉም ታላቁም ታናሹም ቁስለኛ ሆኗል፡፡ ኢሳ.1፤6 ከእግር ጫማ አንስቶ እስከ ራስ ድረስ ጤና የለውም ቍስልና እበጥ የሚመግልም ነው አልፈረጠም፥ አልተጠገነም፥ በዘይትም አልለዘበም። ይህ ማለት መሪውም ተመሪውም የፍቅር ዘይት ጎሎታል በነገር እበጥ ተመትቷል ራሱን ለመጠገን በአንድ የፍቅር ሰንሰለት ውስጥ መግባት አለበት፡፡ እንዲህ ሲሆን ወይንም ለተቀበለነው ዓላማ ታማኝ ሆነናልና ዋጋው ይጠብቀናል፡፡ ብዙ ጊዜ ሰዎች ባለ አንድ ሲባል ትንሽ ነገር አድርገው ይቆጥሩታል ነገር ግን እንደዛ አይደለም እግዚአብሔር ትንሽ ሀብት የለውም፡፡ ትልቁ ሰው ይህን ነገር ሁሉ አድርግ ተብሎ የታዘዘው የፈጣሪ የእጅ ሥራ ነው፡፡ ይህ ትልቅ ሰው መሥራት የሚገባውም ትልቅ ሥራ ነውና ከፍቅርና ከአንድነት የበለጠ ትልቅ ሥራም የለምና፡፡

ከላይ እንዳልነውም ባለሁለቱም እግዚአብሔርን መውደድና ባልንጀራን መውደድ ናቸው፡፡ ሉቃስ.10፤30 እንዲህ ይላል፡- አንድ ሰው ከኢየሩሳሌም ወደ ኢያሪኮ ወረደ በወንበዴዎችም እጅ ወደቀ፤ እነርሱም ደግሞ ገፈፉት ደበደቡትም በሕይወትና በሞት መካከልም ትተውት ሄዱ። ድንገትም አንድ ካህን በዚያ መንገድ ወረደ አይቶትም ገለል ብሎ አለፈ። እንዲሁም ደግሞ አንድ ሌዋዊ ወደዚያ ስፍራ መጣና አይቶት ገለል ብሎ አለፈ። አንድ ሳምራዊ ግን ሲሄድ ወደ እርሱ መጣ አይቶትም አዘነለት፥ ቀርቦም ዘይትና የወይን ጠጅ በቍስሎቹ ላይ አፍስሶ አሰራቸው፥ በራሱ አህያም ላይ አስቀምጦት ወደ እንግዶች ማደርያ ወሰደው ጠበቀውም። በማግሥቱም ሁለት ዲናር አውጥቶ ለባለቤቱ ሰጠና። ጠብቀው፥ ከዚህም በላይ የምትከስረውን ሁሉ እኔ ስመለስ እከፍልሃለሁ አለው። ይህ ነው ፍቅረ ቢጽና ፍቅረ እግዚአብሔር ማለት ሁለት ዲናር ሰጠው ሲል ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው ሆኖ በሞቱ እኛን አድኖ በመጨረሻም የሰጠን ነገር ቢኖር እነኝህ ሁለቱን ነገር ነው፡፡ ትርፋማ ከሆን የምናገኘው ዋጋ ይጠብቀናል ማለት ነው፡፡

ባለ አምስት ሲባል በተፈጥሮ የተቀበልናቸው የስሜት ሕዋሳት የምንላቸው ናቸው፡፡ የተቀበልናቸው በጎ ሥራ ልንሠራባቸው ነው፡፡ አዳም በእነዚህ የስሜት ሕዋሳት በደለ ክርስቶስ በመቸንከርና በሞቱ ካሳ ከፈለለት፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ በቅዳሴው ተናግሮታል አዳምን የፈጠሩ እጆች በመስቀል ላይ ተቸነከሩ በማለት ለሕዋሳቱ በአጠቃላይ የከፈለለትን ዋጋ ይዘረዝራል፡፡ ይህ ማንነት የእኛ ሳይሆን የፈጣሪ ነው፡፡ እኛ አደራ እንደመቀበላችን የተቀበልነውን አደራ በንጽሕና መጠበቅ ነው፡፡ ሕዋሳቶቻችን በምግባር፤ በትሩፋት፤ በጾም ትርፋማ ከሆኑ በዝች በንትሿ በምትጠፋው ዓለም ሳይሆን ለነገው ሰማያዊ ሕይወት ራስን ማዘጋጀት ይሆናል፡፡ በአጭር ለማድረግ እንዳንዱ ሰው እነኝህ ሀብቶች በውስጡ አሉ እስከሠራባቸው ድረስ የማያልፍና የማያልቅ ዋጋ ያገኝባቸዋል በአንጻሩም ካልሠራባቸው ጥያቄ አይቀሬ ነው፡፡ በተቀበልነው ነገር ታማኝ እንድንሆን አምላከ ቅዱሳን ይርዳን፡፡

ይቆየን

ደብረ ዘይት

ደብረ ዘይት

በመጋቤ ሐዲስ ፍቅረ ማርያም ባዘዘው

በቦሌ መንበረ ብርሃን ቅዱስ እግዚአብሔር አብ ቤተክርስቲያን የሐዲስ ኪዳን የትርጓሜ መምህር

 

የዐቢይ ጾም አምስተኛ ሳምንት ደብረ ዘይት በመባል ይጠራል በዚህ ቀን ጌታችንና መድኃኒታች ኢየሱስ ክርስቶስ ስለዓለም ፍጻሜ ወይንም የመጨረሻው የፍርድ ቀን ምን እንደሚመስል ያስተማረበት ቀን ነው፡፡ ይህም  ቀን ደብረ ዘይት በመባል ይታወቃል፡፡ ደብር ማለት ተራራ ሲሆን ዘይት ማለት ደግሞ ወይራ ማለት ነው፡፡ ይህም ማለት ወይራ የበዛበት ተራራ ማለት ነው፡፡ ለዛሬው ርእስ የሚሆነን ድንጋይ በድንጋይ ላይ ሳይፈርስ አይቀርም በሚል ይሆናል፡፡

‹‹አማን እብለክሙ ኢይትኃደግ ዝየ ዕብን ዲበ ዕብን ዘኢይትነሠት››

እውነት እነግራችኋለሁ ድንጋይ በድንጋይ ላይ ሳፈርስ አይቀርም ማቴ. 24፤2

ቃሉም እንዲህ ሲል ይገልጻል፤- ኢየሱስም ከመቅደስ ወጥቶ ሄደ፥ ደቀ መዛሙርቱም የመቅደሱን ግንቦች ሊያሳዩት ቀረቡ። እርሱ ግን መልሶ፦ ይህን ሁሉ ታያላችሁን? እውነት እላችኋለሁ፥ ድንጋይ በድንጋይ ላይ ሳይፈርስ በዚህ አይቀርም አላቸው። እንደግዲህ ከዚህ ገጸ ንባብ የምንመለከተው ስለ አንድ የመቅደስ ድንጋይ የፀሐይ ብርሃን አርፎበት ዐይንን የሚስብና የሚያምር ሆኖ የተመለከቱት ደቀ መዛሙርቱ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስን ድንጋዩን እንዲመለከተው ጋበዙት፡፡ እርሱ ግን ሁሉን የሚያውቅ፤ የሁሉ አስገኝ መሆኑን የዘነጉት ይመስላሉ፡፡ ለመሆኑ ነገሩ የምጻት ነገር ከሆነ ዘንድ ስለመቅደሱ ድንጋይ ለምን ሊነሣ ቻለ? የመቅደሱ ድንጋይ ምንድን ነው፡፡

እንግዲህ የመቅደሱን ድንጋይ ስንመለከት በቁሙ የሰው እጅ የሠራው ሥራ ሁሉ በአዲስ ይሠራል ይተካል በተሻሻለ ሁኔታ ወቅቱ በሚጠብቀው አይነት ሊሠራ ይችላል፡፡ ከዚህ ጋር ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እየተናገረ ያለው ሰው ሰለተባለ መቅደስ ነበር፡፡

ሐዋርያት የፀሐይ ብርሃን ሰፍሮበት አምሮ ለዐይን የሚስብ ሆኖ በተመለከቱት ጊዜ ነበር ጌታችንን ተመለከተው ያሉት፡፡ ስለዚህ መቅደሱ ማን ነው ስንል፡፡

መቅደስ ሰው፡- የመጀመሪያው መቅደስ የእግዚአብሔር ማደሪያ በራሱ አርአያና ምሳሌ የፈጠረው ሰው የተባለው ክቡር ፍጥረት ነው፡፡ የፀሐይ ብርሃን ሰፍሮበት መታየቱ ዕድሜ ነው፡፡ ዕድሜ ፀሐይ ነው፡፡ ደምቆ ይታያል ሁሉንም የምንሠራበት ጊዜ ነው፡፡ ነገር ግን ፀሐይ እንደወጣ አይኖርም ይመሻል ይነጋል በመሆኑን ዕድሜም እንዲሁ ነው፡፡ የሰው ልጅ ይወለዳል፡፡ የፀሐይ ብርሃን የተባለ ውበት፤ ደም ግባት መቅደስ በተባለው ሰውነት ላይ ደምቆ ይታያል እንዲህ እንደሆነ ግን አይኖርም በጊዜው ያልፋል፡፡ ለዚህም መጽሐፈ መክብብ እንዲህ ይላል፡፡

መክ.12-1 የጭንቀት ቀን ሳይመጣ በጕብዝናህ ወራት ፈጣሪህን አስብ ደስ አያሰኙም የምትላቸውም ዓመታት ሳይደርሱ ፀሐይና ብርሃን ጨረቃና ከዋክብትም ሳይጨልሙ፥ ደመናትም ከዝናብ በኋላ ሳይመለሱ ቤት ጠባቆች በሚንቀጠቀጡበት፥ ኃያላን ሰዎችም በሚጎብጡበት፥ ጥቂቶች ሆነዋልና ፈጭታዎች ሥራ በሚፈቱበት፥ በመስኮትም ሆነው የሚመለከቱ በሚጨልሙበት፥ በአደባባይም ደጆቹ በሚዘጉበት ቀን የወፍጮ ድምፅ ሲላሽ፥ ከወፍ ድምፅ የተነሣ ሰው ሲነሣ፥ ዜማም የሚጮኹ ሴቶች ልጆች ሁሉ ዝግ ሲሉ ከፍ ያለውን ደግሞ ሲፈሩ፥ ድንጋጤም በመንገድ ላይ ሲሆን ለውዝም ሲያብብ፥ አንበጣም እንደ ሸክም ሲከብድ፥ ፈቃድም ሲጠፋ ሰው ወደ ዘላለም ቤት ሲሄድ፥ አልቃሾችም በአደባባይ ሲዞሩ የብር ድሪ ሳይበጠስ፥ የወርቅም ኵስኵስት ሳይሰበር፥ ማድጋውም በምንጭ አጠገብ ሳይከሰከስ፥ መንኰራኵሩም በጕድጓድ ላይ ሳይሰበር፥ አፈርም ወደ ነበረበት ምድር ሳይመለስ፥ ነፍስም ወደ ሰጠው ወደ እግዚአብሔር ሳይመለስ ፈጣሪህን አስብ። ይህ ሁሉ የሚነግረን ዕድሜ የተባለ የፀሐይ ብርሃን ሳይጠልቅ ሰው በዚህ ዓለም ምን መሥራት እንዳለበት የሚገልጽ ነው፡፡ ምንም ማማር፤ ውበት ቢኖርም ቅሉ ሁሉን እንዳልነበረ የሚያደርግ የማይለይ ድኀ ባዕለ ጸጋ የማይል ሞት የተባለ ትልቅ ነገርን ተሸክመን ነው የምንኖረው፡፡ ጌታችንም ድንጋይ በድንጋይ ላይ ሳይፈርስ አይቀርም ሲል እንግዲህ ሰው የተባለው መቅደስ ሞቱ አይቀርምና በጎ ሥራ መሥራት እንደለብን የሚገልጽ ነው፡፡ ሰው የሚሞት ከሆነ ለጥቂትም ጊዜ ቢሆን በጎ ሥራ መሥራት ይኖርበታል፡፡ ሥም አይሞትም በጎ ሥራን መቃብር  አይሸፍነውም፡፡ የተፈጠርንበት ለበጎ ዓላማ ከሆነ በጎ ሥራ መሥራትን ገንዘብ ማድረግ ራስን ለታላቅ ክብር ማብቃት ነው፡፡

መቅደስ፡- ድንጋይ በድንጋይ ላይ ሳይፈርስ አይቀርም ሲል ሌላው ምሥጢር ይህ መቅደስ በብሉይ ኪዳን የነበረ መቅደስ ነው፡፡ ነገር ግን በሐዲስ ኪዳን እውነተኛዋ ቤተመቅደስ በክርስቶስ ደም ስለምትታነጸው መቅደስ እየተናገረ ነበር ምክንያቱም የብሉይ ኪዳን መቅደስ የበግ መስዋዕት ቢቀርብባትም ቅሉ ሰው ሊድንበት አልቻለም፡፡ አሁን ግን አማናዊው በግ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱን ቤዛ አድርጎ ከነበረብን የሞት ፍዳ ነጻ አድርጎ ቀራንዮ ላይ መቅደሱን አንጾልናል፡፡ እንዲህ ሲል ስለሐዲስ ኪዳን መቅደስ መሠራት እየነገርን ነበር፡፡

መቅደስ፡- ሌላው ነገር ደግሞ ድንጋይ በድንጋ ላይ ሳይፈርስ አይቀርም ሲባል የሰው ልጆችን የመዳን ምሥጢር የሚናገር ማንነት ያለው ምዕራፍ ነው፡፡ ይህ ሲባል እንደሚታወቀው አዳም ከ 7 ዓመት በኋላ በጥፋቱ ከገነት ተባርሮ ወጥቷል በመሆኑም ባሕርዩ ጎስቋላ ሆኗል፡፡ በአጠቃላይ አዳም የተባለ መቅደስ ሰውነት በኃጢአት ምክንያት ማንነቱን አጥቷል ጌታችን ይህን የተበላሸ ባሕርይ ወይንም ማንነት እንደገና ሊሠራው ሰው ሆኗልና ለዚህ ነበር ድንጋይ በድንጋይ ሳርፈርስ አይቀርም በማለት አዳም የተባለ መቅደስ በኃጢአት ምክንያት ቢፈርስም ዳግመኛ እርሱ ሰው በመሆን አዳም መቅደስን ሠርቶታል ወይንም አንፆታል፡፡ ከዚህ በኋላ ግን ይህ መቅደስ ራሱን ካልጠበቀ ክርስቶስ ዳግመኛ አይሞትለትም፡፡ እርሱ የሚመጣው ይህን ዓለም ለማሳለፍ እንጅ፡፡ ይልቁንም ሰው ራሱን ከኃጢአት ለይቶ በንስሐ በሥጋ ወደሙ ታትሞ ሊኖር ግድ ነው፡፡ በዚሁ ምዕራፍ ቁጥር 19 ላይ እንዲህ ይላል፡- በዚያችም ወራት ለርጉዞችና ለሚያጠቡ ወዮላቸው። ርጉዝና የሚያጠቡ የተባሉ በኃጢአት ውስጥ ያሉ ንስሐ ያልገቡ ኃጢአትን እየሠሩ ምንም ለማይመስላቸው ሰዎች በንስሐ ተዘጋጅተው እንዲኖሩ የተላለፈ ቃል ነው፡፡ እንደሚታወቀው ይህን መቅደስ ለመሥራት የጨረሰባቸው ጊዜ 46 ዓመት ነው ይህ ቁጥር በዕብራይስጥ ራሱን የቻለ አቆጣጠር አለው 46 ሊል የአዳምን ማንነት የያዘ ቁጥር ነው፡፡ ADAM( አዳም) የሚለው በቁጥር ሲያስቀምጡት A አልፋ አንድ ቁጥር ነው D ዴልታ አራት ቁጥር ነው A አልፍ አንድ M May አርባ ነው በአጠቃላይ 46 ይሞላል ማለት ነው፡፡ ይህም ማለት ደግሞ መቅደስ የተባለ አዳም መሆኑን ይገልጻል ማለት ነው፡፡ በአጠቃላይ ኢየሱስ ክርስቶስ በሞቱ አዳም የተባለ መቅደስን ዳግመኛ እንደሠራው የሚናገር ነው፡፡

ይቀጥላል …ይቆየን

መጻጉእ

መጻጉእ

በመጋቤ ሐዲስ ፍቅረ ማርያም ባዘዘው

በቦሌ መንበረ ብርሃን ቅዱስ እግዚአብሔር አብ ቤተክርስቲያን የሐዲስ ኪዳን የትርጓሜ መምህር

 

‹‹አልብየ ሰብእ›› ሰው የለኝም ዮሐንስ ወንጌል 5፤7

እንደሚታወቀው የዐቢይ ጾም አራተኛ ሳምንት መጻጉእ በመባል ይጠራል፡፡ ይህም ማለት በዕለቱ 38(ሠላሳ ስምንት) ዓመት በደዌ ምክንያት በአልጋ ላይ ተጣብቆ ይኖር የነበረ ሰው የተፈወሰበት ዕለት በመሆኑ መጻጉእ በመባል ይታወቃል፡፡

የዛሬው የዕለቱ ትምህርታችን ሰው የለኝም በሚል ይሆናል፡፡ ወንጌሉ እንዲህ ሲል ይገልጸዋል፡- በኢየሩሳሌምም በበጎች በር አጠገብ በዕብራይስጥ ቤተ ሳይዳ የምትባል አንዲት መጠመቂያ ነበረች፤ አምስትም መመላለሻ ነበረባት። በእነዚህ ውስጥ የውኃውን መንቀሳቀስ እየጠበቁ በሽተኞችና ዕውሮች አንካሶችም ሰውነታቸውም የሰለለ ብዙ ሕዝብ ይተኙ ነበር። አንዳንድ ጊዜ የጌታ መልአክ ወደ መጠመቂያይቱ ወርዶ ውኃውን ያናውጥ ነበርና፤ እንግዲህ ከውኃው መናወጥ በኋላ በመጀመሪያ የገባ ከማናቸው ካለበት ደዌ ጤናማ ይሆን ነበር። በዚያም ከሠላሳ ስምንት ዓመት ጀምሮ የታመመ አንድ ሰው ነበረ፤ ኢየሱስ ይህን ሰው ተኝቶ ባየ ጊዜ፥ እስከ አሁን ብዙ ዘመን እንዲሁ እንደ ነበረ አውቆ ልትድን ትወዳለህን? አለው። ድውዩም። ጌታ ሆይ፥ ውኃው በተናወጠ ጊዜ በመጠመቂያይቱ ውስጥ የሚያኖረኝ ሰው የለኝም ነገር ግን እኔ ስመጣ ሳለሁ ሌላው ቀድሞኝ ይወርዳል ብሎ መለሰለት። ኢየሱስ፦ ተነሣና አልጋህን ተሸክመህ ሂድ አለው፡፡ ወዲያውም ሰውዬው ዳነ አልጋውንም ተሸክሞ ሄደ፡፡በዚህ ምዕራፍ ውስጥ ትልቅ የምንማረው ነገር አለ ያም 38 ዓመት በአልጋ ተጣብቆ የሚኖር ሰው እግዚአብሔር ከእርሱ ጋራ ሲሆን መፈወሱን ነው፡፡ ሰዎች ለምን ሰው የለንም እንዲሉ ያደርጋቸዋል?

  1. ከደረሰባቸው ወይንም ከአጋጠማቸው ችግር አኳያ፡- ብዙ ጊዜ ሰው ከባድና ውስብስብ ነገር ሲገጥመው በአንጻሩም አለኝ የሚለው ሰው ከጎኑ ሲርቅ ከተስፋ መቁረጥ የተነሣ ሰው የለኝም ይላል፡፡ መጻጉእም 38 ዓመት ከአልጋ የተኛው ከሚጠመቅበት ቦታ የሚያደርሰው ሰው ባለማግኘቱ ተስፋ በወቁረጥ ሰው የለኝም ሲል ተደምጧል፡፡ እንደሚታወቀው የእግዚአብሔር መልአክ ውኃውን ወይንም መጠመቂያውን ከእግዚአብሔር ታዝዞ ያናውጠው (ይቀድሰው)  ነበር ያኔ አስቀድሞ የሚገባ ከደዌው ወይንም ከበሽታው ይፈወስ ነበር፡፡ በአንጻሩም ደግሞ ሰው የሌለው ከዛው ተኝቶ ይኖራል እንጅ የመፈወስ ዕድሉ አነሳ ነበር፡፡ መጻጉእ እንዲህ ባለ ሕይወት ውስጥ ሆኖ ነገር ግን ወደ መጠመቂያው የሚወስደው ሰው ያጣ ምስኪን ሰው ነበር፡፡ መጻጉእ ስሜትን የሚነካ ነገር የተናገረው ከነበረው የውስጥ ጉዳት የተነሣ ነበር፡፡ ለመሆኑ ስንት አይነት ደዌ ወይንም በሽታ አለ? እንደ አባቶቻችን አስተምህሮ ወደ አራት አይነት ደዌ አሉ ከእነዚህም መካከል ደዌ ዘኃጢአት፤ደዌ ዘመቅሰፍት፤ ደዌ ዘንጽሕ፤ ደዌ ዘዕሴት ናቸው፡፡ ደዌ ዘንጽሕ እንደ ጢሞቴዎስ ከማስተማር የተነሣ ሰውነታቸው ደርቆ የነበር ስለንጽሕናቸው የተቀበሉት ደዌ ነው ያም ማለት ለክብር የሚያበቃ ነው፡፡ ደዌ ዘዕሴትም እንደ ኢዮብ ነው እርሱም ዋጋ ያገኘበት በሽታ ወይንም ደዌ ነበር፡፡ ደዌ ዘመቅሰፍት እንደ ሄሮድስ በጥፋቱ በመቅሰፍት የሞተበት ነው፡፡ ደዌ ዘኃጢአት ደግሞ መጻጉእ እንደታመመበት ያለ ደዌ ወይንም በሽታ ነበር፡፡ መጻጉእ ሲጀመር ደዌው ከእግዚአብሔር ህግ በመውጣቱ ወይንም የእግዚአብሔርን ትዕዛዝ በመተላለፉ የመጣበት ደዌ ነበር፡፡ እንደሚታወቀው በብሉይ ኪዳን ሰው ኃጢአት ሲሠራ በሰውነቱ ደዌው ወይንም በሽታው ይታይ ነበር፡፡ በሐዲስ ኪዳን ግን ሰው ኃጢአት ሲሠራ በንስሐ የሚመለስ ሆኗል፡፡ እንግዲህ መጻጉእ 38 ዓመት በሙሉ ብቻውን ሆኖ የሰው ያለህ ሲል የቆየው ምን አልባትም ደዌው የእግዚአብሔርን ትዕዛዝ በመተላለፍ ያጋጠመው በሽታ በመሆኑ ዘመዶቹ በሙሉ ስለተውት ወይንም አናውቅህም ስላሉት እንዲሁም ዘመድ እያለው ነገር ግን ከእርሱ ስለራቁ ተስፋ በመቁረጥ ዘመድ የለኝም ሲል ተደመጠ፡፡ ዓለም እንዲህ ነው ሁሉም ነገር ሲኖርህ ሲሞላልህ ሰው የሚፈልገው ነገር ሁሉ ከአንተ ሲኖር ዘመደ ብዙ ትሆናለህ ሁሉም ሲያልቅ ግን ሁሉም ይቆማል፡፡
  2. በእግዚአብሔር አለመተማመን፡-  ብዙ ጊዜ ሰው የሚመካው በዘመዱ ወይንም በሀብቱ ሲሆን ይስተዋላል ነገር ግን ሁሉም ነገር ያልፋል፡፡ ሰው በዘመዱ ተስፋ አድርጎ ሁሉም ነገር አልሆን ሲል ወደ ማይሆን ሕይወት ውስጥ ሲገባ ይስተዋላል፡፡ ይህ ሁል ነገር የሚመጣው በእግዚአብሔር አለመተማመን የሚያመጣው ችግር ነው፡፡ትልቁ የሰው ልጆች እምነት በእግዚአብሔር ከሆነ ጥያቄያችን በሙሉ ወዲያውኑ መልስ ያገኝ ነበር፡፡ ቅዱስ ወንጌል እንዲህ ይላል፡- ዕብ.11፤5-7 ሄኖክ ሞትን እንዳያይ በእምነት ተወሰደ፥ እግዚአብሔርም ስለ ወሰደው አልተገኘም። ሳይወሰድ እግዚአብሔርን ደስ እንዳሰኘ ተመስክሮለታልና፤ ያለ እምነትም ደስ ማሰኘት አይቻልም፤ ወደ እግዚአብሔር የሚደርስ እግዚአብሔር እንዳለ ለሚፈልጉትም ዋጋ እንዲሰጥ ያምን ዘንድ ያስፈልገዋልና። ኖኅ ገና ስለማይታየው ነገር ተረድቶ እግዚአብሔርን እየፈራ ቤተሰቦቹን ለማዳን መርከብን በእምነት አዘጋጀ፥ በዚህም ዓለምን ኰነነ፥ በእምነትም የሚገኘውን ጽድቅ ወራሽ ሆነ። እግዚአብሔርን የምናስደስትበትና ለጥያቄያችን መልስ የምናገኘው በእምነት ነው፡፡ ቅዱሳን አባቶቻችን በአስቸጋሪ ሕይወት ውስጥ ያለፉት በእምነት ነው፡፡ እምነት ካለ መንገዳችን ሁሉ ቀና ይሆናል ለጥያቄያችን በቶሎ መልስ እናገኛለን፡፡ በአንጻሩም እምነት የሌለውና በሰው ወይንም በገንዘቡ የሚተማመን ሰው ከወደቀበትና እንዲሁም ከመጣበት የሕይወት ፈተና ውስጥ በቶሎ ሊነሳ አይችልም፡፡ መጻጉእ በአልጋ ላይ የተኛ 38 ዓመት ነው፡፡ ይህ ማለት ደግሞ መጻጉእ የታመመ ወይንም ደዌው የያዘው ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው ከመሆኑ በፊት ነው ማለት ነው፡፡ ምክንያቱም ጌታችን በዚህ ምድር የኖረው 33 ዓመት ነው፡፡ እንግዲህ ለሚያስተውል ሰው 38 ዓመት የተኛን ሰው በአንድ ቀን ተንሥና አልጋህን ተሸክመህ ሂድ ሲባል ምን ይሰማናል? ለእርሱ ሁሉም ይቻላል፡፡ ክቡራን እና ክቡራት ዛሬ ሰው ሁሉ ሳይታመም የታመመ ሆኗል ብቻውን ያወራል ከህሊናው ጋር ይታገላል፡፡ የሰው ሁሉ ሕይወት ፍጹም በእግዚአብሔር የመተማመኑ ነገር ደብዝዟል፡፡ መመካት በሚገባው አምላክ ደፍሮ እርሱ ይረዳኛል ሲል አይስተዋልም፡፡ ይልቁንም ሌላ ተጨማሪ ነገር አስቀምጦ በእግዚአብሔር እንደሚተማመን ብቻ በአንደበቱ ያወራል ውስጡ ግን የለም፡፡ ሁሉንም ነገር የሚያደርገው አማራጭን ይዞ ነው፡፡ ፀበል ለመፀበል ሲፈልግ ማን ይሻላል ብሎ ዕጣ አውጥቶ ነው፡፡ በአጠቃላይ እግዚአብሔር ያደርጋል የሚለው እምነት የጠፋ ይመስላል፡፡ ሰውን ተስፋ አድርጎ እንዲህ ሆንኩ ከማለት በእግዚአብሔር ተማምኖ የሚሰጠውን ነገር በተስፋ መጠባበቅ ይበልጣል፡፡ በእግዚአብሔር ፍጹም መተማመናችን የሚታወቀው የምንፈልገውን ነገር በትዕግሥት ደጅ ስንጸና ብቻ ነው፡፡ ሃይማኖት ያለው ሰው ትዕግሥት  ገንዘቡ ነች፡፡ ክርስቶስ ይህን ዓለም ሲያድን በትዕግሥት ውስጥ አልፎ ነው፡፡ በድለንም እንኳ በትዕግሥት ነው የተመለከተን፡፡ ዛሬም እንዲሁ፡፡ የሚገርመው ነገር ደግሞ ሰው አጥፍቶ እግዚአብሔር ዝም ሲለው አጥፍቼ ለምን ዝም አልከኝ አይልም በአንጻሩ ደግሞ ጥያቄ ጠይቆ እግዚአብሔር ሲታገስ ለምን ዝም አልክ ይላል፡፡ እግዚአብሔር አጥፍተን ለምን ዝም አለን? ስለማያቀውቅ ነው? ምክንያቱ እግዚአብሔር ሰው ከነ ኃጢአቱ እንዲጠፋ አይፈልግምና ነው፡፡ ጥያቄያችንም እንዲሁ ነው፡፡ እግዚአብሔር ትእግሥትኛ በመሆኑ ለጥያቄያችን መልስ እያለው ነገር ግን ከእኛ ትዕግሥትን ይፈልጋል፡፡ እርሱ ለሚሰጠው ነገር ጉድለት የለበትምና በትዕግሥት ሆነን ከጠየቅነው ሁሉኑም በጊዜው ያውም የሚጠቅመንን ያድርግልናል፡፡

ይቆየን ይቀጥላል

 

ምኩራብ

ምኩራብ

 

በመጋቤ ሐዲስ ፍቅረ ማርያም ባዘዘው

በቦሌ መንበረ ብርሃን ቅዱስ እግዚአብሔር አብ ቤተክርስቲያን የሐዲስ ኪዳን የትርጓሜ መምህር

 

የዐቢይ ጾም ሦስተኛ ሳምንት ምኩራብ በመባል ይጠራል ይህም ስያሜ የተሰጠው ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዕለቱ ከሠራው ሥራ አንጻር ነው፡፡ ለዛሬው ለትምህርታችን መነሻ የምናደርገው የቤትህ ቅናት በላኝ በሚል ይሆናል፡፡

‹‹ቅንዓተ ቤትከ በልዓኒ›› የቤትህ ቅናት በላኝ፡፡ መዝ. 68(69) ፤10

ቤት ሲባል ማደሪያ ወይንም ቤት ለእኛ ሁለንተናችን ነው ማለት ይቻላል:: ሰው ከድካም የሚያርፍበት በአጠቃላይ ቤት ብዙ ነገር የያዘ ለሰው ልጅ ከመሠረታዊ ፍላጎቶቹ መካከል አንዱና ዋነኛው ነው፡፡ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ዕለት ወደ መኩራብ በመሄድ በኃጢአት የተበላሸውን ቤት ያስተካከለበት ቀን ነው፡፡ ከዚህ አንጻር የእግዚአብሔር ቤት ማን ወይም ምንድን ነው የሚለውን ነገር የምንማርበት ነው፡፡

 

ቤቱ ማን ነው

መመስገኛው፡ ይህን ስንል የሰው ልጅ በዚህ ምድራዊ ሕይወቱ እያለ ከፈጣሪው ጋር በጸሎት፤ በእንባ የሚገኛኝበት ቤት ነው ይህም ቤተ መቅደስ ወይንም በዛሬው አጠራር ቤተ ክርስቲያን ወይንም የክርስቲያን ቤት ክርስቲያኖች በአንድነት እግዚአብሔርን ለማመስገን የሚሰበሰቡበት ቤት ማለት ነው፡፡ እንግዲህ በዛሬው ዕለት በብሉይ ኪዳን የነበሩ ሰዎች መቅደሱን መመስገኛ መሆኑን ዘንግተው መለወጫ፤ መሻሻጫ አድርገውት ስላገኘ ቤቴ የፀሎት ቤት ነው እንጅ የወንበዴ ዋሻ አይደለም በማለት ሥራቸውን ሁሉ የነቀፈበትም ብቻ ሳይሆን ጅራፍ አንስቶም የገረፈበትም ቀን ነው፡፡ የእግዚአብሔር ቤት ንጹሕ ነው በንጽሕና ሆነን ልናገለግልበትም ልንገለገልበትም  ይገባል ምክንያቱም ሲያጠፉ የተገሰጹበትን ያህል በጎ ለሚሠሩ ደግም በአንጻሩ ምን ያህል ክብር እንደሚያገኙበት ግልጽ ነው፡፡ መቼም ቢሆን መጥፎ ነገር አድርጎ ከመወቀስ እንዲሁም በህሊና ከመፀፀት  ይልቅ በጎ ነገር ሠርቶ በረከትንና ሰላምን ማግኘት ለሁሉም ሰው የሚበጅ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ሰው ወደ እግዚአብሔር ቤት የሚሄደው ሰላምን፤ በረከትን፤ ዕድሜን እንዲሁም የአገርን ሰላም ለመለመንና ለመማፀን ነው፡፡ እንዲህ ያለው ቤት በነጋዴዎች ተሞልቶ ሲመለከት ጌታችን ጅራፍ አዘጋጅቶ ሊገርፍ ጀመር፡፡ በእርግጥ ያኔ የሚታይ ወይንም ሰው በአይኑ የሚያየው ጅራፍ ነው፡፡ ሰው በጅራፍ ቢገረፍ የውጭ ቁስል ነው ከጥቂት ጊዜ በኋላ ቁስሉ ሊሽር ወይንም ሊድን ይችላል፡፡ ወገኖቼ ዛሬ ዛሬ ደግሞ ሰው ሁሉ በውጭ በምንሠራው በደል ውስጣችን የህሊና ቁስለኛ ሆኗል፡፡ የማይድን ቁስል ማለት ይህ ነው፡፡ ለእግዚአብሔር ቤት ጥንቃቄ ያስፈልገዋል፡፡ እንዲህ በፍርሃተ እግዚአብሔር ሆነን ለምናደርገው ነግ ደገሞ ፀፀጽና ወቀሳ የለበትም በረከትና ሰላም እንጅ፡፡ የዕለቱ ወንጌል ዮሐ.2፤12 እንዲህ ይላል  ከዚህ በኋላ ከእናቱና ከወንድሞቹ ከደቀ መዛሙርቱም ጋር ወደ ቅፍርናሆም ወረደ፥ በዚያም ጥቂት ቀን ኖሩ። የአይሁድ ፋሲካም ቀርቦ ነበር፥ ኢየሱስም ወደ ኢየሩሳሌም ወጣ። በመቅደስም በሬዎችንና በጎችን ርግቦችንም የሚሸጡትን ገንዘብ ለዋጮችንም ተቀምጠው አገኘ፤ የገመድም ጅራፍ አበጅቶ ሁሉን በጎችንም በሬዎችንም ከመቅደስ አወጣቸው፥ የለዋጮችንም ገንዘብ አፈሰሰ ገበታዎቻቸውንም ገለበጠ፥ ርግብ ሻጪዎችንም። ይህን ከዚህ ውሰዱ፤ የአባቴን ቤት የንግድ ቤት አታድርጉት አላቸው። ደቀ መዛሙርቱም። የቤትህ ቅናት ይበላኛል ተብሎ እንደ ተጻፈ አሰቡ። የእግዚአብሔርን ቤት ያከበረ ሁሉ እርሱ ይከብራል፡፡

  1. ቤት የተባለ ሰው ነው፡-

ሰው በእግዚአብሔር አርአያና ምሳሌ የተፈጠረ ክቡር ፍጥረት ነው፡፡ ዘፍ.1፤26 እግዚአብሔርም አለ፦ ሰውን በመልካችን እንደ ምሳሌአችን እንፍጠር የባሕር ዓሦችንና የሰማይ ወፎችን፥ እንስሳትንና ምድርን ሁሉ፥ በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱትንም ሁሉ ይግዙ። ይህ ሰው ክብር ነው፡፡ በእግዚአብሔር አርአያ መፈጠር ብቻ ሳይበቃው ሁሉን እንዲገዛ ስልጣን ተሰጠው እንጅ፡፡ ይህ ክቡር ፍጥረት ራሱን ባለመሆን ከእርሱ ተፈጥሮ ውጭ የሆኑትን በምንም ነገር የማይመስሉትን አራዊት እንስሳትን ለመምሰል ራሱን አዋረደ፤ ክብርና ጌጡ ልብስ ሆኖ እያለ ልብሱን በመራቆት እስሳትን መሰለ በእግዚአብሔር አርአያና ምሳሌ የተፈጠረውን ማንነቱን ወይንም የእግዚአብሔርን ቤት በዝሙት አፈረሰ፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ እንዲህ ይላል፡- 1ኛቆሮ. 6፤15-20 ሥጋችሁ የክርስቶስ ብልቶች እንደ ሆነ አታውቁምን? እንግዲህ የክርስቶስን ብልቶች ወስጄ የጋለሞታ ብልቶች ላድርጋቸውን? አይገባም። ወይስ ከጋለሞታ ጋር የሚተባበር አንድ ሥጋ እንዲሆን አታውቁምን? ሁለቱ አንድ ሥጋ ይሆናሉ ተብሎአልና። ከጌታ ጋር የሚተባበር ግን አንድ መንፈስ ነው። ከዝሙት ሽሹ። ሰው የሚያደርገው ኃጢአት ሁሉ ከሥጋ ውጭ ነው፤ ዝሙትን የሚሠራ ግን በገዛ ሥጋው ላይ ኃጢአትን ይሠራል። ወይስ ሥጋችሁ ከእግዚአብሔር የተቀበላችሁት በእናንተ የሚኖረው የመንፈስ ቅዱስ ቤተ መቅደስ እንደ ሆነ አታውቁምን? በዋጋ ተገዝታችኋልና ለራሳችሁ አይደላችሁም፤ ስለዚህ በሥጋችሁ እግዚአብሔርን አክብሩ። የእግዚአብሔር ማደሪያ የሆነው የእኛ ሰውነት በዝሙት፤ በኃጢአት ሲበላሽ እግዚአብሔር ለቤቱ የሚቀናው ቅናት ከባድ ነው ምክንያቱም ቤቱ  የባለቤቱ የእግዚአብሔር እንጅ የእኛ አይደለምና፡፡ እኛ ሰዎች ይህን ቤት የተቀበልነው በአደራነት ነው፡፡ አደራውን የጠበቀ ዋጋው ይጠብቀዋል፡፡ በዚህ ዓለም የምንኖር ሰዎች ቤታችንን እንዴት በንጽሕና እንደምንይዘው እንዲያውም ሰው እንደምንቀጥርለት እኛው ራሳችን ምስክሮቹ ነን፡፡ ይህ ቤት የዛሬ ቤት ነው አይከተለንም ከሞት አያድነንም እስካለን ብቻ የምንኖርበት ቤት ነው፡፡ ለዚህ ቤት እንዲህ የምጨነቅለት ከሆነ ይህን ዓለም አሳልፎ በትንሳኤ ዘጉባኤ ለሚነሣው የእግዚአብሔር ቤት ለሆነው ማንነታችን ምን ልንሠራለት ይገባል ብለን እራሳችንን ልንጠይቅ ይገባል፡፡ ቤቱ ሲፈርስ የማያድሰው ማነው? እንዲያውም ከቻለም አዲስ ቤት የተሸለ ቤት ሊሠራ ይችላል እንደ ሀብቱ መጠን፡፡ እግዚአብሔር የእርሱ ቤት በመሆናችን ስተን ከገነት ስንወጣ ዳግመኛ ሠራን፤ ቤቱ አደረገን ይህም የሆነ እንዲሁ ሳይሆን በመጀመሪያ በዓለም ውስጥ ድንግል ማርያም እርሷ በንጽሕና የተሸለመች ሆና በመገኘቷ ከእርሷ ራሱን ዝቅ አድርጎ ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስ ነሳ፤ ተወለደ፤ ግብጽ ተሰደደ፤ ተጠመቀ፤ገዳም ገብቶ ጾመ፤ አስተማረ፤ቀራንዮ ላይ ተቸንክሮ በመስቀል ላይ ዋለ፤ሞተ፤ተቀበረ፤ከሙታን ተነሣ፤ በ40ኛው ቀን አረገ፤ዳግመኛም ይመጣል፡፡ ይህ ሁሉ የተደገረው የእግዚአብሔር ቤት ለተባለ ለሰው ነው፡፡ ለቤቱ እንዲህ ዋጋ ተከፈለ ያውም የሞት ዋጋ፡፡ እግዚአብሔር እኛን ከፈጠረበት ጥበቡ ይልቅ እኛን ያዳነበት ጥበቡ ይልቃል፡፡ ሲፈጥረን ከመሬት አፈርን አንስቶ ነፍስን እም ኀበ አልቦ ማለትም ለነፍስ ምክንያት ሳይኖራት አዋሕዶ ፈጠረን ሲያድነን ግን መስቀል ላይ ተችንክሮ አዳም ላጠፋበት ሕዋሳት ሳይቀር ዋጋ ከፍሎ ነው፡፡

አዳም በእጆቹ ኃጢአት ሠርቶ ነበር ኢየሱስ ክርስቶስ እጁን ተቸነከረ

በእግሮቹ ኃጢአት ሠርቶ ነበር እግሮቹን ተቸነከረ

በአፉ ዕፀ በለስን በመብላት ኃጢአት ሠርቶ ነበር እርሱ በአፉ ሆምጣጤ ተቀበለ

በጀሮው በድሏል እርሱም በጀሮው የአይሁድን ሽሙጥ ሰማ

በአጠቃላይ አዳም ለሠራባቸው ሕዋሳት በሙሉ አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ካሳ ከፍሏል ምክንያቱም ቤቱ የእርሱ ቤት ነውና የእኛ አይደለም፡፡ እያንዳንዱ ሰው በዚህች አጭርና በማትረባው ዓለም ውስጥ ጠብቅ ተብሎ የተሰጠውን የአደራ ቤት ሲዘሙትበት፤ ሲያጭበረብርበት ሲታይ ሁሌም ነዋሪ የማይሞት ዘለዓለማዊ ይመስላል፡፡ ግን ሁሉም ወደ መጣበት አፈር ይመለሳል፡፡ በመሆኑም ሰው የእግዚአብሔር ቤት የሆነውን ማንነቱን ጠብቆ ካቆየ በመጨረሻ ሰዓት ከፈጣሪው ጋር በፍቅር ይኖራል፡፡

ቸርነቱን ያብዛልን ወላዲተ አምላክ በምልጃዋ አትለየን

 

ይቆየን

 

 

 

 

 

ቅድስት

                                              ቅድስት

በመጋቤ ሐዲስ ፍቅረ ማርያም ባዘዘው

በቦሌ መንበረ ብርሃን ቅዱስ እግዚአብሔር አብ ቤተክርስቲያን የሐዲስ ኪዳን የትርጓሜ መምህር

 

የዐቢይ ጾም ሁለተኛው ሳምንት ቅድስት ይባላል፡፡ ይህም ሲባል በአጠቃላይ ሁሉም ሳምንታት ከተሰየመላቸው አንዱ ነው ማለት ነው፡፡ ይህም ቅድሰት ሲባል የተለየ ወይንም የከበረ የሚለውን ትርጉም የሚሰጥ ሲሆን ይህ ማለት ግን ሌሎች ቀኖች የተለዩ ወይንም የከበሩ አይደሉም ማለት አይደለም ፡፡ የዕለቱ ስያሜ ነው እንጂ፡፡ በዚህ ቀን የሚነበበው ወንጌል እንዲሁም የዕለቱ ምስባክ ዕለቱን በተመለከተ የሚነበቡ ወይንም የሚነገሩ ናቸው፡፡ ለዛሬው  ርእስ የምናደርገው በማቴዎስ ወንጌል ያለውን ነው ይህም በዕለቱ የሚነበበው ወንጌል ነው፡፡

‹‹ወሶበ ትጸውሙ ኢትኩኑ ከመ መደልዋን›› በምትጾሙበት ጊዜ እንደ ግብዞች አትሁኑ ማቴ.6፤16

ጾም ማለት ማቆም ወይንም መከልከል ማለት ነው፡፡ ሰው ጾምን ሲጾም የሚከለከልባቸው ነገሮች አሉ፡፡ ፍትሐ ነገሥት አንቀጽ 15 አንድ ሰው ሰው ጾመ ሲባል ከምን ከምን መከልከል አለበት ሲባል፡፡

ከምግብ ይህንም ፍትሐ ነገሥት አንቀጽ 15 ጾም ማለት በታወቀ ጊዜና በታወቀ ሰዓት ከመብልና ከመጠጥ የምንከለከለው መከልከል ነው ሲል ይገልጸዋል፡፡ በታወቀ ጊዜ ሲባል ሰባቱን አጽዋማት ማለት ሲሆን በታወቀ ሰዓት ሲባል ጾመን የምንቆይበትን ሰዓት ሲገልጽልን ነው፡፡ ይህንም ዘጠኝ ሰዓት ይላል ምክንያቱም አንድ የኦርቶዶክስ አማኝ ውሎ አስቀድሶ ሥጋወደሙን መቀበል ስላለበት ነው ፡፡ የአንድ አማኝ የኦርቶዶክስ ልጅ ሕይወቱ ከሥጋ ወደሙ የተለየ አይደለም፡፡ ከሥጋ ወደሙ የተለየ ሰው ተሸናፊ ነው፤፤ ያገኘው ጠላት ሁሉ (የአጋንንት ሠራዊት) ያሸንፈዋል በፍትወተ ሥጋ ሀሳብ ይሸነፋል፡፡ በሥጋ ወደሙ የታተመ ማንነት ያለው ሰው ግን ድል ይነሳል እንጅ ድል አይነሳም፡፡ ራዕይ 7፤9-17 እንዲህ ይላል፡፡ ከዚህ በኋላ አየሁ፥ እነሆም፥ አንድ እንኳ ሊቆጥራቸው የማይችል ከሕዝብና ከነገድ ከወገንም ከቋንቋም ሁሉ እጅግ ብዙ ሰዎች ነበሩ፤ ነጭ ልብስም ለብሰው የዘንባባንም ዝንጣፊዎች በእጆቻቸው ይዘው በዙፋኑና በበጉ ፊት ቆሙ፤ በታላቅም ድምፅ እየጮሁ። በዙፋኑ ላይ ለተቀመጠው ለአምላካችንና ለበጉ ማዳን ነው አሉ። መላእክቱም ሁሉ በዙፋኑና በሽማግሌዎቹ በአራቱም እንስሶቹ ዙሪያ ቆመው ነበር፤ በዙፋኑም ፊት በግምባራቸው ተደፉ፥ ለእግዚአብሔርም እየሰገዱ። አሜን፥ በረከትና ክብር ጥበብም ምስጋናም ውዳሴም ኃይልም ብርታትም ከዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ ለአምላካችን ይሁን፤ አሜን አሉ። ከሽማግሌዎቹም አንዱ ተመልሶ፦ እነዚህ ነጩን ልብስ የለበሱ እነማን ናቸው? ከወዴትስ መጡ? አለኝ። እኔም። ጌታ ሆይ፥ አንተ ታውቃለህ አልሁት። አለኝም። እነዚህ ከታላቁ መከራ የመጡ ናቸው፥ ልብሳቸውንም አጥበው በበጉ ደም አነጹ። ስለዚህ በእግዚአብሔር ዙፋን ፊት አሉ፥ ሌሊትና ቀንም በመቅደሱ ያመልኩታል፥ በዙፋኑም ላይ የተቀመጠው በእነርሱ ላይ ያድርባቸዋል። ከእንግዲህ ወዲህ አይራቡም፥ ከእንግዲህም ወዲህ አይጠሙም፥ ፀሐይም ትኵሳትም ሁሉ ከቶ አይወርድባቸውም በዙፋኑ መካከል ያለው በጉ እረኛቸው ይሆናልና፥ ወደ ሕይወትም ውኃ ምንጭ ይመራቸዋልና፤ እግዚአብሔርም እንባዎችን ሁሉ ከዓይናቸው ያብሳል። ይህ ነው የማይጠፋ ማንነት በሥጋ ወደሙ የታተመ በጾም የተወሰነ፡፡ ሰው ሲጾም ሲፀልይ ሕይወቱ ከሥጋ ወደሙ ጋር የታተመ ነው፡፡

2 ቅዱስ ያሬድ ይጹም ዓይን፤ ይጹም ልሳን፤ ይጹም አፍ፤ ዕዝንኒ ይጹም እምሰሚዓ እሱም፡፡ ዓይን ይጹም አንደበት ይጹም አፍ ይጹም ጀሮም መጥፎ ነገር ከመስማት ይከልከል ይላል፡፡ በአጠቃላይ ጾም ሲባል መላ ሰውነታችን ነው የሚጾመው ማለት ነው፡፡ ቅድስት የተባለም ለዚህ ነው፡፡ የተለየ ጾም፤የተለየ ማንነት፤ የተለየ ስብእና ሊኖረን የሚችለው እንዲህ ያለ እውነተኛ ጾም ስንጾም ነው፡፡ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ክብር ይግባውና በማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 5፤6 ላይ እንዲህ ሲል አስተምሮ ነበር፡፡ ዛሬ ስለጽድቅ የሚራቡ ብጹዓን ናቸው ይጠግባሉና፡፡ እንግዲህ ዛሬ ስንል የዕኛ ዘመን ነው፡፡ ዛሬ ዕድሜ ነው፤ ዛሬ የተባለ ወጣቱም የእርሱ ዕድሜ አሁን ያለበት ዛሬ ይባላል፡፡ ሁሉም ሰው አሁን ያለበት ዕድሜ ለእርሱ ዛሬ ነው፡፡ ዛሬ በዕድሜው ሥራን የሚሠራ የሚጾም የሚፀልይ ዋጋ አለው፡፡ የሚገርመው ነገር ደግሞ እርሱ ባለቤቱ ዛሬ የሚራቡ እያለ እየተናገረ ለነገ የምናስብ ብዙ በመሆናችን ነው፡፡ ዛሬ መሥራት ስንችል፤ ዛሬ መስገድ ስንችል በአጠቃላይ ማኛውንም መንሰሳዊ ነገር ዛሬ ማድረግ ስንችል ሁሉንም ነገር ለነገ እንላለን እኛ የምናውቀው ዛሬን እንጅ ነገን አይደለም፡፡ ነገ ሌላ ነውና፡፡ ሁሉም ሰው መንፈሳዊን ተግባር ዛሬ መፈጸም አለበት ነገ በመጨረሻው ሰዓት ዋጋው ይጠብቀው ዘንድ፡፡ ሰው ሁለንተናው ሲጾም ለደከመበት ዋጋው ይሰጠዋል ብዙ ጊዜ እየጾሙ ነገረኛ የሆኑ ወንድሞቻቸውን የሚያስቀይሙ በሐሜት የሚኖሩ ብዙ ሰዎች አሉ አንደበታቸው ሁሉ ሲጾም ነው ዋጋ የሚያገኙት፡፡

  1. እውነተኛ ፍርድን በመስጠት፡- ኢሳይያስ 58፤1 በኃይልህ ጩኽ፥ አትቈጥብ፥ ድምፅህን እንደ መለከት አንሣ፥ ለሕዝቤ መተላለፋቸውን ለያዕቆብ ቤትም ኃጢአታቸውን ንገር። ነገር ግን ዕለት ዕለት ይሹኛል መንገዴንም ያውቁ ዘንድ ይወድዳሉ ጽድቅን እንዳደረጉ የአምላካቸውንም ፍርድ እንዳልተዉ ሕዝብ እውነተኛውን ፍርድ ይለምኑኛል፥ ወደ እግዚአብሔርም ለመቅረብ ይወድዳሉ። ስለ ምን ጾምን፥ አንተም አልተመለከትኸንም? ሰውነታችንንስ ስለ ምን አዋረድን፥ አንተም አላወቅህም? ይላሉ። እነሆ፥ በጾማችሁ ቀን ፈቃዳችሁን ታደርጋላችሁ፥ ሠራተኞቻችሁንም ሁሉ ታስጨንቃላችሁ። እነሆ፥ ለጥልና ለክርክር ትጾማላችሁ በግፍ ጡጫም ትማታላችሁ ድምፃችሁንም ወደ ላይ ታሰሙ ዘንድ ዛሬ እንደምትጾሙት አትጾሙም። እኔ የመረጥሁት ጾም ይህ ነውን? ሰውስ ነፍሱን የሚያዋርደው እንደዚህ ባለ ቀን ነውን? በውኑ ራሱን እንደ እንግጫ ዝቅ ያደርግ ዘንድ ማቅንና አመድንም በበታቹ ያነጥፍ ዘንድ ነውን? በውኑ ይህን ጾም፥ በእግዚአብሔርም ዘንድ የተወደደ ቀን ትለዋለህን? እኔስ የመረጥሁት ጾም ይህ አይደለምን? የበደልን እስራት ትፈቱ ዘንድ፥ የቀንበርንስ ጠፍር ትለቅቁ ዘንድ፥ የተገፉትንስ አርነት ትሰድዱ ዘንድ፥ ቀንበሩንስ ሁሉ ትሰብሩ ዘንድ አይደለምን? እንጀራህንስ ለተራበ ትቈርስ ዘንድ፥ ስደተኞቹን ድሆች ወደ ቤትህ ታገባ ዘንድ፥ የተራቈተውንስ ብታይ ታለብሰው ዘንድ፥ ከሥጋ ዘመድህ እንዳትሸሽግ አይደለምን? የዚያን ጊዜ ብርሃንህ እንደ ንጋት ይበራል፥ ፈውስህም ፈጥኖ ይበቅላል፥ ጽድቅህም በፊትህ ይሄዳል፥ የእግዚአብሔርም ክብር በኋላህ ሆኖ ይጠብቅሃል። የዚያን ጊዜ ትጠራለህ እግዚአብሔርም ይሰማሃል ትጮኻለህ እርሱም፦ እነሆኝ ይላል። ከመካከልህ ቀንበርን ብታርቅ፥ ጣትህንም መጥቀስ ብትተው፥ ባታንጐራጕርም፥ ነፍስህንም ለተራበ ብታፈስስ፥ የተጨነቀውንም ነፍስ ብታጠግብ፥ ብርሃንህ በጨለማ ይወጣል ጨለማህም እንደ ቀትር ይሆናል። እግዚአብሔርም ሁልጊዜ ይመራሃል ነፍስህንም በመልካም ነገር ያጠግባል አጥንትህንም ያጠናል አንተም እንደሚጠጣ ገነት፥ ውኃውም እንደማያቋርጥ ምንጭ ትሆናለህ። ከዱሮ ዘመን የፈረሱት ስፍራዎች ይሠራሉ፥ የብዙ ትውልድም መሠረት ይታነጻል አንተም። ሰባራውን ጠጋኝ፥ የመኖሪያ መንገድን አዳሽ ትባላለህ። ፈቃድህን በተቀደሰው ቀኔ ከማድረግ እግርህን ከሰንበት ብትመልስ፥ ሰንበትንም ደስታ፥ እግዚአብሔርም የቀደሰውን ክቡር ብትለው፥ የገዛ መንገድህንም ከማድረግ ፈቃድህንም ከማግኘት ከንቱ ነገርንም ከመናገር ተከልክለህ ብታከብረው፥ በዚያን ጊዜ በእግዚአብሔር ደስ ይልሃል፥ በምድርም ከፍታዎች ላይ አወጣሃለሁ፥ የአባትህንም የያዕቆብን ርስት አበላሃለሁ የእግዚአብሔር አፍ ተናግሮአልና።

ትክክለኛ ጾም ከሆነ ዋጋ አለው ያለበለዚያ ድግሞ ያስወቅሳል ማለት ነው ሰውን እያስለቀሱ የሚጾሙት ጾም ከባድ ሰለሆነ ሁላችንም በፍቅር መጾም እንዳለብን ነው የሚነገረን፡፡ ለዚህ ጾም ክርስቶስን ወልዳ ምክንያት የሆነችን ወላዲተ አምላክ በምላጃዋ አትለየን አሜን፡፡

 

ይቆየን፡፡

 

 

 

ዘወረደ

እንኳን ለታላቁ ጾም በሰላም አደረሳችሁ

በአጠቃላይ ዐቢይ ጾም ስምንት ሳምንታት ሲኖረው ከዚህም የመጀመሪያም ዘወረደ በመባል ይታወቃል ሁሉም ሳምንታት የራሳቸው የሆነ መጠሪያ አላቸው ሁሉንም በተራ እንመለከታቸዋለን ለዛሬው ግን የመጀመሪያውን ሳምንት እንመለከታለን፡፡

 

ዘወረደ

በመጋቤ ሐዲስ ፍቅረ ማርያም ባዘዘው

በቦሌ መንበረ ብርሃን ቅዱስ እግዚአብሔር አብ ቤተክርስቲያን የሐዲስ ኪዳን የትርጓሜ መምህር

 

ዘወረደ ሲባል እንግዲህ የግዕዝ ቃል ነው ወረደ ማለት ከላይ ወደታች መጣ ወይንም ወረደ ማለት ሲሆን ዘወረደ ሲል የመጣ ወይንም የወረደ ማለት ነው፡፡ እንገዲህ የመጀመሪያው የጾም ሳምንት ዘወረደ በማለት ይጀመራል ለምን ሲባል ከልዕልና ወደ ትሕትና ወይንም ከዙፋኑ ወደ ተዋረደው ሰው የመጣውን አምላክ የምናስብበት ዕለት ነው፡፡ ምክንያቱም እርሱ ሰው በመሆኑ ወይንም ከድንግል ማርያም በመወለዱ የወደቀውን ወይንም ክብር ያጣውን ሰው ወደ ክብሩ ይመለሰው ዘንድ ወዷልና፡፡ እርሱ ሰው ካልሆነ የሰው ልጆች መዳን አይፈጸምምና፡፡ ለዚህም ነው ዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 3፤11-15 ባለው ንባብ ውስጥ አካላዊ ቃል ወደዚህ ዓለም መምጣቱን ሲናገር እንዲህ ይላል ወአልቦ ዘዐርገ ውስተ ሰማይ ዘእንበለ ዘወረደ እምሰማይ ወልደ ሕጓለ እመሕያው፡፡ ወደሰማይ የወጣ የለም ወደ ሰማይ የወጣው ከሰማይ የወረደው የሰው ልጅ ክርስቶስ ነው በማለት ከድንግል ማርያም ነፍስና ሥጋን ተዋሕዶ ወደሰማይ ማረጉን ይገልጻል፡፡ ዘወረደ ማለት ይህ ነው፡፡ ከሰማይ የወረደ ወደ እኛ የመጣ እርሱ አካላዊ ቃል ነው፡፡ መዝ.39፤1 እግዚአብሔርን ደጅ ጸናሁት እርሱም ዘንበል አለልኝ ይላል፡፡ ይህ ማለት ከአዳም ጀምሮ የነበረው የሰው ልጅ በሙሉ እርሱ ሰው እንዲሆን በጾም በፀሎት የተማጸኑበት ልመና ወይን ፀሎት ነው ዘንበል አለልኝ ሲል ሰው ሆነልኝ ወደ እኔ መጣ የእኔን ደካማ አካል ነሣ ማለት ነው፡፡ እንግዲህ ዘወረደ ሲባል ይህ ነው ሰው ሰለሆነው አምላክ የምንማርበት ርእስ ነው፡፡

አምላክ ለምን ሰው ሆነ የወደቀውንና የጎሰቆለውን የሰው ልጅ ከዙፋኑ እንዳለ ለምን አያድነውም ነበር፡፡ ይህ ትልቅ ትምህርት የምንማርበት ርእስ ነው፡፡ በዘፍጥረት ምዕራፍ 3፤22 ላይ ሰው ስለመሆኑ አስቀድሞ ተነገሮ ነበር ያም ማለት እርሱ ሰው ሆኖ እኛን የእርሱ ልጆች አደረገን፡፡ ፍቅሩን አየን ቸርነቱን ቀመስን፡፡ እርሱ ዝቅ በማለቱ ሰማያዊው አምላክ ምድር መውረዱ እኛ ምን መሥራት እንዳለብን ተማርን፡፡ በተለይም የክርስትና ጉዞ ለሰው የምንኖርበት ሕይወት መሆኑን ተማርንበት፡፡ እርሱ ለጠፋው አንድ በግ ወደ እኛ መጣ ብዙ የባዘኑ፤ የሕወትን መንገድ የሳቱ፤ ከሕይወት ይልቅ ሞትን የመረጡ፤ በተሳሳተ መንገድ እየተጓዙ የእውነት መንገድ የሚመስላቸው፤ ከእግዚአብሔር ፈቃድ ይልቅ የራሳቸው የሀሳብ ፈቃድ ያሸነፋቸው ብዙ ሰዎች አሉ፡፡ እርሱ ለእኛ ሰው ከሆነ እኛ ለእኛነታችን ሕይወት ሕይወት መሆን እንዴት ተሳነን፡፡ እርሱ ከሰማይ ወረደ እኛ ግን ሁላችንም  ከምድር ወይንም ከመሬት ተፈጥረን መሬቱ መሬትነቱን ናቀው፡፡ዘፍጥረት 2፤7 እግዚአብሔር አምላክ ሰውን ከምድር አፈር ሠራው ይላል፡፡ ሀቁና ውነታው ይህ ሆኖ እያለ መሬት መሬትን ሲንቀው ሁሉም ወደመሬት ሲመለሱ ማየት እንዴት ያማል፡፡ የሰው ማንነቱ የሚታወቅው ከእግዚአብሔር ጋር ሲኖር ብቻ ነው፡፡ እግዚአብሔር ያለው ሁሉም አለው እግዚአብሔር የሌለው ግን ሁሉም ነገር የለውም፡፡ ቢኖረውም ቅሉ በትካዜ የሚያልቅ ነው፡፡ ሰውን ማክበር ዝቅ ማለት እግዚአብሔርን ማየት ነው፡፡ እርሱ ለእኛ ዝቅ ብሏልና፡፡ በዚሁ ዕለት የሚሰበከው ምስብካም የሚያዘን ይህን ነው፡፡

‹‹ተቀነዩ ለእግዚአብሔር በፍርሃት

ወተሐሰዩ ሎቱ በረዓድ

አጽንዕዋ ለጥበብ ከመ ኢይትመዐዕ እግዚአብሔር››

ለእግዚአብሔር በፍርሃትና በመንቀጥቀጥ ደስ እያላችሁ ተገዙለት እግዚአብሔር እንዳይቆጣቸሁ ጥበብን አጽንታችሁ ያዟት፡፡ጥበብ ማለትም በጎ ምግባር፤ ፍቅር፤ትሕትና፤ የመሳሰሉት ናቸው፡፡ በአጠቃላይ እግዚአብሔር ያደረገልን በሙሉ ጥበብ ነው፡፡ እርሱም ጥበብ ይባላል፡፡ ዲዮስቆሮስ በቅዳሴው አይቴ ብሔራ ለጥበብ፡፡ የትበብ አገሯ ወዴት ነው በማለት ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ይናገራል፡፡በእርግጥ በንጹሕ ልብ በተሰበረ መንፈስ ውስጥ ያለ ሰው እርሱ የእግዚአብሔር ማደሪያ ሊሆን ይችላል፡፡ በአጠቃላይ ጥሩ ስብእና ባለው ሰውነት ውስጥ እግዚአብሔር ሥራን ይሰራል እመብርሃን ወላዲተ አምላክ የሆነቸው ከዓለም ተለይታ መገኘቷ ነው እኛ እኮ የእርሷ ልጆች ነን፡፡ እርሷም የእኛ እናት ናት መስቀል ሥር የተቀበልናት ልዑል እግዚአብሔር ሰው የሆነባት፤ ዓለምን ያዳነባት፡፡ ሁላችንም በሃይማኖት ጸንተን እንድንኖር ቸርነቱ ይርዳን አሜን

ይቆየን

 

ከተራ ማለት ምን ማለት ነው?

ከተራ ማለት ምን ማለት ነው?

አቅራቢ  መጋቢ ጥበብ ኤርሚያስ ባዬ

በየዓመቱ የጥምቀት በዓል በድመቀት ይከበራል፡፡ ከበዓሉ በፊት የከተራ በዓል የሚከበርበትን ታሪካዊና ሃይማኖታዊ ገለጻ ከተራ ከበበ ካለው የግእዝ ግሥ የወጣ ነው፡፡ ፍችው ውኃ መከተር፣ መገደብ ማለት ነው፡፡ የጥምቀት ዋዜማ ታቦተ ሕጉ ከቤተ መቅደስ ወጥቶ ውኃ ባለበት አካባቢ ስለሚያድር የየአጥቢያው ሕዝብ እየተሰበሰበ በወንዝ ዳር ወይም በምንጭ አካባቢ ድንኳን ይተከላል፡፡ ድንኳንም ከሌለ ዳስ ሲጥል ይውላል፡፡ የምንጮች ውኃ ደካማ በመሆኑ እንዲጠራቀም ይከተራል ጉድጓድ እየተቆፈረ ውኃው እንዳይሄድ ይገደባል፡፡ ketera 2 2“ከተራ” በመባል የሚታወቀው- ዋዜማው” ሠርግው /1981፣8/ እንደገለጹት “ከተራ” የሚለው ቃል “ከተረከበበ ካለው የግዕዝ ግስ የወጣ ነው፡፡ ከተራ ፍቺውም ውኃ መከተር፣ ወይም መገደብ ማለት ነው፡፡” ብለው ሲፈቱ፣ ደስታ ተከለ ወልድ /1962፣ 694/ ደግሞ የጥምቀት ዋዜማ፣ ጥር 10 የጠራ ወራጅ ውኃ የሚከተርበት ታቦትና ሰው ወደ ዠማ ወንዝ የሚወርዱበት ጊዜ” ነው በማለት ይፈቱታል፡፡

ኪዳነ ወልድ ክፍሌም /1948፣ 555/ ከተረ የሚለውን ቃል በቁሙ፣ “ዘጋ፣ አቆመ፣ አገደ፣ ከለከለ፡፡” ማለት ነው ብለው ይፈቱታል፡፡ በየዓመቱ ጥር 10 ቀን የምእመናኑ አብዛኛው ሥራ ውኃውን መከተርና መገደብ በመሆኑ ዕለቱ ከተራ የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል፡፡ ውኃው የሚከተረው በማግሥቱ ጥር 11 ቀን የጥምቀት በዓል ስለሚከበር ለሕዝቡ መጠመቂያ እንዲሆን ነው፡፡ በየሰበካው ቦታ ተለይቶና ተከልሎ ታቦታቱ በዳስ ወይም በድንኳን የሚያድሩበት፣ የተለያዩ የውኃ አካላት ተጠርገው የሚከተሩበት ወይም ሰው ሠራሽ የግድብ ውኃ የሚበጅበት ስፍራ ‹‹ባሕረ ጥምቀት››፣‹‹የታቦት ማደርያ›› እየተባለ ይጠራል፡ ባሕር፡- የውኃ መሰብሰቢያ (ምእላደ ማይ፣ የውኃ መከማቻ (ምቋመ ማይ) ነው፡፡ በሌላ አነጋገር ‹‹የውኃ አገር›› /መካነ ማይ፣ዓለመ ማይ/ ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በቅዱስ ላልይበላ ዘመነ መንግሥት በኢትዮጵያ ምድር እየተመላለሱ በብሕትውና እና በስብከተ ወንጌል ያገለግሉ የነበሩት ጻድቁ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ በአክሱም፣ በመቐለና በመርጡለ ማርያም እየተዘዋወሩ ባሕረ ጥምቀቱን ባርከዋል፡፡ በዐፄ ይኩኖ አምላክ ዘመነ መንግሥት (1260-1275 ዓ.ም) በጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት (1203-1204 ዓ.ም) አሳሳቢነት የተጀመረው ሥርዐተ በዓል ተጠናክሮ እንዲቀጥል በዐዋጅ ትእዛዝ አስተላልፈዋል፡፡

ታቦታቱም በሕዝብ ጥበቃና ክብካቤ ተደርጎላቸው በየጥምቀተ ባሕሩ እንዲያድሩ ወስነዋል፡፡ የበዓሉ አከባበር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሰፋና አድማሱ ብሔራዊነትን እየያዘ መጣ፡፡ ከዐፄ ገብረ መስቀል ጀምሮ የአደባባይ በዓል የሆነው የጥምቀት በዓል በ15ኛው ክ/ዘመን በደገኛው ኢትዮጵያዊው ንጉሠ ነገሥት ዐፄ ዘርዓ ያዕቆብ(1426-1460 ዓ.ም) አማካኝነት ታቦታቱ ወደ ወንዝ ወርደው ዕለቱን እንዳይመለሱ፣ በዚያ ፈንታ በጥምቀት ዋዜማ ጥር 10 ቀን ከሰዓት በኋላ ወደ ባሕረ ጥምቀቱ ወርደው እንዲያድሩ፣ አገሩን በኪደተ እግር ይባርኩም ዘንድ በሄዱበት መንገድ እንዳይመለሱ በዐዋጅ ወሰኑ፡፡ ይህን ታሪክ በመከተል ዐፄ ናዖድ (1486-1500) ዓ.ም) ማንኛውም የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ምእመን ታቦተ ሕጉ ወደ ባሕረ ጥምቀቱ በሚወርድበት እና ከባሕረ ጥምቀቱ ወደ ቤተ መቅደሱ በሚመለስበት ጊዜ አጅቦ አውርዶ፣ አጅቦ መመለስ እንዳለበት በዐዋጅ አስነግረው ነበር፡፡ ሕዝቡም ታቦታተ ሕጉን በሆታና በእልልታ ከቤተ መቅደስ አጅቦ ከአወጣ በኋላ በባሕረ ጥምቀት ከትሞ ማደር ጀመረ ።/ ሐመር ጥር/የካቲት 1998 ዓ.ም/ ketera 3ታቦታት ከአንድ በላይ ሆነው ወደ ከተራው ስለሚሄዱ እግዚአብሔር አምላክ ለነብዩ ሙሴ “የታቦት መኖር ከእናንተ ጋር የመኖሬ ምልክት ነው” ዘፀ 25÷1 እንዳለው ታቦተ ሕጉን ተሸክመው ዮርዳኖስን እንደ ተሻገሩት ካህናተ ኦሪት፤ ካህናቱ የማይለወጠውን ታቦተ ሕጉን በራሳቸው ተሸክመው የብሉዩን ሥርዓት ከሐዲስ ኪዳን ጋር አንድ አድርገው የሐዲስ ኪዳን መሠረት ኢየሱስ ክርስቶስን እያሰቡ፤ ካህናተ ሐዲስም ወደ ከተራ (ዮርዳኖስ) ይጓዛሉ፡፡

ሊቃውንቱም እንዲሁ ለበዓሉ የሚስማማውን ቃለ እግዚአብሔር እያደረሱ እንደሚያድሩ ሊቀ ጠበብት ሐረገወይን አገዘ ያስረዳሉ። ሊቀ ጠበብት አያይዘውም የከተራ ዕለት ጥር 10 ቀን ኢየሱስ ክርስቶስ በዮሐንስ እጅ ለመጠመቅ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ ወንዝ የሄደበትን ለማዘከር ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ኃዳፌ ነፍስ ለጻድቃን የሚለውን ዋዜማ ይቆማሉ፡፡ የዋዜማው ቀለም ከቀኑ በአራት ሰዓት በመላው አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ይጀመራል ከዚያም የዋዜማው ሥርዐት ቅዱስ ተብሎ እስከ ሰላም ያለው ቀለም ይደርሳል፡፡ በዕለቱም ቅዳሴ ይቀደሳል፡፡ ታቦተ ሕጉን የሚያነሡት ሰሞነኛ ካህን ከምግበ ሥጋ ተከልክለው ለዕለቱ የሚገባውን ጸሎት ያደርሳሉ፡፡ በከተራው ዕለት ድንኳን ተተክሎ፣ ዳሱ ተጥሎና ውኃው ተከትሮ ሁሉም ነገር ከተስተካከለ በኋላ ታቦተ ሕጉ የሚንቀሳቀስበት ሰዓት ሲደርስ የየቤተ መቅደሱ ታቦታት በወርቅና በብር መጎናጸፊያ እየተሸፈኑ በተለያየ ኅብር በተሸለሙ የክህነት አልባሳት በደመቁ ካህናትና የመጾር መስቀል በያዙ ዲያቆናት ከብረው፣ ከቤተ መቅደስ ወደ አብሕርት / ምጥማቃት/ ለመሄድ ሲነሡ መላው አብያተ ክርስቲያናት የደወል ድምፅ ያሰማሉ፡፡ ምእመናን ከልጅ እስከ ዐዋቂ በዐጸደ ቤተ ክርስቲንና ታቦታቱ በሚያልፉባቸው መንገዶች ‘’ለጥምቀት ያልሆነ ቀሚስ …’’ እንደሚባለው ያማረ ልብሳቸውን ለብሰው በዓሉን ያደምቃሉ፡፡ ሊቀ ጠበብት የበዓሉን ሂደት ሲገልጹ ታቦቱ ከመንበረ ክብሩ ሲነœ ‹‹ዮም ፍስሀ ኮነ››ተብሎ ከተጸነጸለ በኋላ ታቦቱ ወጥቶ ወረደ ወልድ እምሰማያት ውስተ ምጥማቃት የሚለው ሰላም በሊቃውንቱ ይዘመራል፣ ይጸነጸላል፣ ይመላለሳል፡፡

የወርቅ ካባና ላንቃ የለበሱ ቀሳውስት፣ መነኮሳት ጥላ የያዙት ከታቦቱ ጎን መስቀልና ጽና የያዙት ከታቦቱ ፊት ይሄዳሉ፡፡ እንደ ቀሳውስቱ ተመሳሳይ ልብሰ ተክህኖ የለበሱት ዲያቆናት ጥላ፣ መስቀልና ቃጭል ይዘው እያቃጨሉ ከቀሳውስቱ ፊት በመሆን ያጅቧቸዋል፡፡ ከነዚህም ሌላ ካባ፣ ላንቃ ጥንግ ድርብ የለበሱ መዘምራን የብር፣ የነሐስ መቋሚያና ጸናጽል ይዘው ‹‹ወረደ ወልድ›› የሚለውን አመላለስ እያሸበሸቡ ዲያቆናቱን ቀድመው ይሄዳሉ፡፡ የደብር አለቆችና አበው ካህናት ታቦቱን ተከትለው ይጓዛሉ፡፡ የሰንበት ት/ቤት ተማሪዎችም በተለያዩ ቀለማት ባሸበረቁ አልባሳት ተውበው ትርዒት እያሳዩ “ወረደ ወልድ፣ እግዚኡ መርሐ፣ ሆረ ኢየሱስ” እና ሌሎችንም የአማርኛ መዝሙራትን እየዘመሩ፣ እናቶች “ነይ ነይ እምዬ ማርያም” እያሉ ሌሎችም ምስጋናዎችም እየቀረቡ ጉዞ በዝግታ ወደ ጥምቀተ ባሕር ይሆናል፡፡የከተራ በዓል ማክበሪያ ቦታ እንደደረሱ ታቦታቱ በድንኳኑ አጠገብ ቆመው ‹‹ወረደወልድ›› የሚለው ሰላም ተመርቶ በአግባቡከተለዘበ በኋላ ጸሎት ተደርጎ የዕለቱ ትምህርተ ወንጌልና ዝማሬ ከቀረበ በኋላ ውዳሴ ማርያም፣ መልክዐ ኢየሱስ ተደግሞ ታቦታ ሕጉ ወደ ተዘጋጀላቸው ድንኳን ይገባሉ /ሠርግው፤ 1981፣ 9/፡፡ በሁለተኛ የአገልግሎት ክፍል ካህናቱ ስብሐተ እግዚአብሔር ሲያደርሱ ያድራሉ፡፡ በመንፈቀ ሌሊትም ሥርዐተ ቅዳሴው ተጀምሮ ከሌሊቱ በ9፡00 ሠርሆተ ሕዝብ ይሆናል፡፡ በነጋታው የሥርዐተ ጥምቀቱ መርሐ ግብር ይቀጥላል፡፡

የከተራ በዓል ምሳሌያት በበዓለ ጥምቀት ዋዜማ የታቦታቱ ወደ ወንዝ መውረድና የባሕረ ጥምቀቱ መዘጋጀት ሃይማኖታዊ ታሪክና ምሳሌ አለው፡፡የቃል ኪዳኑን ታቦት አክብሮ መጓዝና ወደ ወንዝ መወረድ የተጀመረው በአሮን ልጅ በአልዓዛር ጊዜ ነው፡፡ ኢያሱ በሙሴ እግር ተተክቶ ሕዝበ እስራኤልን እየመራ ከዮርዳኖስ ወንዝ ሲደርስ ባሕሩ ከሁለት ይከፈልና ወራጁም ይቆም/ ይከተር/ ነበር፡፡ እስራኤል ዘሥጋ ወደ ምድረ ርስት ለመግባት የዮርዳኖስን ወንዝ ሲሻገሩ፡- ድንኳን ጥለው የቃል ኪዳኑን ታቦት በድንኳን ውስጥ አድርገው ሌዋውያኑ በዙሪያው፣ ካህናቱ ደግሞ በውስጥ ኾነው እግዚአብሔርን እያመሰገኑ አድረው በማለዳ ተሻግረዋል /ኢያሱ 3÷8-9/፡፡ ካህናቱ የቃል ኪዳኑን ታቦት አክብረው የወንዙን ዳርቻ በረገጡት ጊዜ እንደ ክረምት ማዕበል ይወርድ የነበረው ውኃ ግራና ቀኝ ተከፍሎ እንደ ግድግዳ ወደ ላይ ቆሟል፡፡ ሕዝቡ ተሻግሮ እስከሚያበቃ ታቦተ ጽዮንን ያከበሩት ካህናት ከወንዙ መሀል ይቆሙ ነበር፡፡ በዚህ መሠረት ‹‹ወተጠምቃ እገሪሆሙ ለካህናት›› ይህም‹‹የካህናት እግሮቻቸው የዮርዳኖስን ውኃ በመርገጣቸው እንደ ጥምቀት ሆናቸው›› በሐዲስ ኪዳነ ጌታችን ለመሠረተው ሥርዐተ ጥምቀት ምሳሌ ነበር፡፡ ቤተ ክርስቲያናችን የጥምቀትን ዋዜማ ከተራ ብላ የጠራችው ከዚህ በመነሣት ነው፡፡ ጌታችን በተጠመቀ ጊዜ የዮርዳኖስ ወንዝ የላይኛው ሸሽቶ ወደ ላይ ተመልሶ ሽቅብ ፈሷል፡፡ የታቹም ወደ ታች ሸሽቷል፡፡ የላይኛው ፈሳሽ ተቋርጦ እንደ ክምር ተቆልሎ ቀርቷል።ቅዱስ ዳዊት የተመለከተውም ይህንኑ ነው። ከአዳም ጀምሮ እስከ ክርስቶስ ድረስ በዘር ይወርድ የነበረው ፍዳ መርገም በክርስቶስ ቤዛነት ተቋርጦ ፤ የታቹም ፈጽሞ መድረቁ ኃጢአተ አዳም የመጥፋቱ ምሳሌ ነው፡፡ እስራኤል ፈለገ ዮርዳኖስን ተሻግረው ወደ ኢያሪኮ መሔዳቸው ምእመናን በጥምቀት ከኃጢአት ቍራኝነት ተላቀው እግራቸውን ወደ ልምላሜ ገነት ወደ ዕረፍት መንግሥተ ሰማያት አቅንተው ለመሔዳቸው ምሳሌ ነው፡፡

ኢያሱ የጌታ፣ እስራኤል የምእመናን፣ ዮርዳኖስ የጥምቀት፣ ምድረ ርስት የገነት መንግሥተ ሰማያት ምሳሌ ነው፡፡ ታቦቱን አክብሮ የሚሔደው ካህን የቅዱስ ዮሐንስ፣ታቦቱ የጌታችን፣ ባሕረ ጥምቀቱ የዮርዳኖስ ወንዝ፣ ታቦታቱን አጅበው የሚሔዱትና በዓሉን የሚያከብሩት ምእመናን ወደ ቅዱስ ዮሐንስ እየመጡ የንስሐ ጥምቀት ሲጠመቁ የነበሩት ሰዎች ምሳሌዎች ናቸው፡፡ ታቦታቱ በጥምቀት ዋዜማ ከመንበራቸው ወደ ጥምቀተ ባሕር መውረዳቸውና በዚያ ማደራቸው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በእደ ዮሐንስ በፈለገ ዮርዳኖስ ከማታው ጀምሮ መውረዱንና ተሰልፎ ተራውን ሲጠብቅ ማደሩን ያጠይቃል፡፡ ‹‹ጥምቀት የሞቱና የትንሣኤው ምሳሌ ነው፡፡ ከኃጥአን ጋር ተቆጥሮ እንዲጠመቅና እንዲሰቀል የተጻፈውን ቃል ንስሐና ጥምቀት የማያስፈልገው ሲሆን ነገር ግን ፍጹም ኃጥእ መስሎ በዮሐንስ እጅ ጥምቀትን ለመፈጸም በማየ ዮርዳኖስ እግር ተጠመቀ፡፡›› /ኪ.ወ.ክ ፤517/፡፡ ጌታችን የተጠመቀበት ወርኀ ጥር በእስራኤላውያን ዘንድ የዝናብ፣ የበረዶ ወራት ነው፡፡ ከወንዝ ዳር ያለ መጠለያ መዋልና ማደር አይቻልም፡፡ በመኾኑም ከዮሐንስ ለመጠመቅ የሚሄዱ ሰዎች ሁሉ በዮርዳኖስ ዙሪያ ድንኳናቸውን ተክለው ያርፉ ነበር፡፡ በዚህ አንጻር ዛሬም በባሕረ ጥምቀት ዙሪያ ድንኳኖች ዳሶች ይጣላሉ፡፡እኛ በዚህ ወቅት ታቦት ይዘን፣ ከወንዝ ወርደን፣ ድንኳን ተክለን በማክበራችን ይፈጸማል፡፡

መልካም የጥምቀት በዓል

በዓለ ጥምቀት

በዓለ ጥምቀት

 

ጥምቀት አጥመቀ አጠመቀ (ነከረ) ከሚለው የግዕዝ ቃል የወጣ ሲሆን ትርጉሙም መጠመቅ መነከር ማለት ነው:: በዚህም ምስጢር ከእግዚአብሔር በመንፈስ እንወለዳለን ::

የጥምቀት ምሳሌ በብሉይ ኪዳን ተጠቅሶ ይገኛል::

  1. የሕዝበ እስራኤል ቀይ ባሕርን መሻገር:: <<ሁሉም በባህር መካከል ተሻገሩ ሁሉም ሙሴን ይተባበሩ ዘንድ በደመናና በባህር ተጠመቁ>> 1 ቆሮ 10:2 ዘጸ 14:22
  2. ኖህና ቤተሰቡ በእምነት መርከብ ሰርተው ከጥፋት ውኃ መዳናቸው 1 ጴጥ 3: 20-21
  3. በኢያሱ የምስፍንና ዘመን የእግዚአብሔርን የቃል ኪዳን ታቦት የተሸከሙት የካህናት እግሮች በውሃ ዳር ሲጠልቁ ከላይ የሚወርደው ውሃ ቆሞ እስራኤል ዮርዳኖስን በደረቅ መሻገራቸው 2 ኢያ 3፡15

ከዚህ ቀጥለን የወልድን ጥምቀት (ጥምቀተ ወልድ) እናያለን

ጌታችን ከእመቤታችን በኅቱም ድንግልና ተጸንሶ በኅቱም ድንግልና ተወለደ:: በተወለደ በ 40 ቀኑ ዕጉለ ርግብ ዘውገ መዕነቅ ይዞ ቤተ እግዚአብሔር በመግባት በመውጣት ሕገ መጽሐፋዊን ሕገ ጠባዕያዊን ሲፈጽም ‘በበህቅ ልህቀ እንዘ ይትኤዘዝ ለአዝማዲሁ እንተ ይእቲ እሙ’ እንዲል (ሉቃ 2:51):: ለእናቱ እየታዘዘ አድጎ 30 ዓመት ሲሞላው ወደ ዮርዳኖስ ሄደ:: ዕለቱ ማክሰኞ ሰዓቱ 10 ሰዓት ሌሊት ነው:: ዮሐንስን አጥምቀኝ አለው:: ዮሐንስም ጌታዬ እኔ ባንተ ልጠመቅ ይገባኛል እንጅ አንተ በእኔ አንዴት ትጠመቃለህ አለው::ጌታም መልሶ ሕግን ሁሉ ልንፈጽም ይገባናልና አለው:: አንድም ጥምቀት አንዲት መሆኗን ያመለክታል::

ዮሐንስም መልሶ ሌላውን በአንተ ስም አጠምቃለሁ አንተን በማን ስም ላጥምቅህ አለው:: ጌታችንም እንዲህ አለው ‘ወልዱ ለቡሩክ ከሣቴ ብርሃን ተሣሃለነ’ እያልክ አጥምቀኝ አለው:: ዮሐንስም እሺ አለ:: ጌታችንም ሊጠመቅ ከዮርዳኖስ ባህር ውስጥ ሲገባ የነቢዩ ቃል ይፈጸም ዘንድ ዮርዳኖስ ወደ ኋላ ሸሸች በመዝሙር 113:5 ‘ባህርኒ ርእየት ወጎየት ወዮርዳኖስኒ ገብአ ድኅሬሁ አድባር አንፈርአጹ ከመሐራጊት። ትርጉም ‘አንቺ ባሕር የሸሸሽ አንቺም ዮርዳኖስ ወደ ኋላሽ የተመለሽ ምን ሆነሻል:: እናንተም ተራሮች እንደኮርማዎች ኮረብቶችሽ እንደጊደር ለምን ዘለላችሁ’ የተባለው የነቢዩ ቃል ይፈጸም ዘንድ::

ጌታ ሲጠመቅ ተራሮች ሽቅብ ዘለሉ ውሆች ተናወጹ የመጣው ፈጣሪያቸው አምላካቸው ነውና:: በኋላ ግን በሰውነቱ ተናግሮ በአምላክነቱ አጽንቷቸው በእደ ዮሐንስ ተጠመቀ:: ተጠምቆ ከውሃ ሲወጣ በማቴ 3:13 -17 እንደተጻፈው አብ በደመና ሆኖ ‘ዝንቱ ውእቱ ወልድየ ዘአፈቅር ሎቱ ስምዕዎ’ የምወደው ልጄ ይህ ነው እርሱን ስሙት ብሎ የባህርይ ልጅነቱን መስክሮለታል:: መንፈስ ቅዱስም በአምሳለ ርግብ ፀዓዳ ሆኖ ወርዶ በራሱ ላይ አርፎበታል::

፩. ከፍ ብሎ በ 31 ዝቅ ብሎ በ 29 ዓመት አለመጠመቁ በ 30 ዓመቱ መጠመቁ አዳም የ 30 ዓመት ጎልማሳ ሆኖ በ 40 ቀን አግኝቶ ያጣትን ልጅነት ለማስመለስ ነው::

፪. አምላክ ሰው ሲሆን በሰው እጅ መጠመቁ ትህትናውን ለመግለጽ ነው::

፫. ዮሐንስን አስጠርቶ ካለበት ቦታ መጠመቅ ሲችል ዮሐንስ ወዳለበት ወደ ገሊላ ሄዶ መጠመቁ ሥርዓትን ለማስተማር ነው:: ምክንያቱም ዮሐንስን አስጠርቶ ተጠምቆ ቢሆን ኖሮ ዛሬ መኳንንቱ መሳፍንቱ ባለስልጣናቱ እቤታችን ድረስ መጣችሁ አጥምቁን ባሉ ነበር::

፬. በማር በወተት መጠመቅ ሲችል በውሃ የተጠመቀበት ምክንያት ማር ሲልሱት ወተትም ሲጠጡት እንጅ ሊታጠቡባቸው አልተፈጠሩምና:: አንድም በማር በወተት ተጠምቆ ቢሆን ኖሮ ማርና ወተትን ድሆች ስለማያገኟቸው ሳይጠመቁ ይቀሩ ነበርና:: ጥምቀት የተሰራ ለሁሉም ሰው ነውና ደሃውም ሀብታሙም በሚያገኘው በውሃ ተጠመቀ:: አንድም በውሃ የተጠመቀበት ምክንያት ውሃ ቢጠጡት ያረካል በታጠቡበት ያነጻል ጥምቀትም ከኃጢአታችን ያነጻናልና:: ጥምቀትም ከሥላሴ መወለዳችንን ቁልጭ አድርጎ ያሳያልና::

፭. ብዙ ባሕር እያለ የዮርዳኖስን ባሕር የመረጠው የዕዳ ደብዳቤያችንን ሊያጠፋልን ነው:: ምክንያቱም ዲያብሎስ አዳምና ሔዋንን የጨለማ መጋረጃ ጋርዶ ‘አዳም ገብሩ ለዲያብሎስ ሔዋን ዓመቱ ለዲያብሎስ’ ብላችሁ ጽፋችሁ ብትሰጡኝ አገዛዜን አቀልላችሁ ነበር ሲላቸው ይህንን ጽፈው ሰጡት:: ዲያብሎስ ያንን በሁለት ቀርጾ ጽፎ አንዱን በዮርዳኖስ አንዱን በሲኦል ጥሎት ነበርና በዮርዳኖስ የጣለውን እንደሰውነቱ ረግጦ እንደምላክነቱ አቅልጦ አጥፍቶልናል:: በሲኦል የጣለውን ጌታ በዕለተ ዐርብ በተሰቀለ ጊዜ በአካለ ነፍስ አጥፍቶልናል:: ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ <<በጥምቀትም ከእርሱ ጋር ተቀብራችሁ በጥምቀት ደግሞ ከሙታን ባስነሣው በእግዚአብሔር አሠራር በማመናችሁ ከእርሱ ጋር ተነሣችሁ። እናንተም በበደላችሁና ሥጋችሁን ባለመገረዝ ሙታን በሆናችሁ ጊዜ ከእርሱ ጋር ሕይወትን ሰጣችሁ። በደላችሁን ሁሉ ይቅር አላችሁ። በእኛ ላይ የነበረውን የሚቃወመንንም በትእዛዛት የተጻፈውን የዕዳ ጽሕፈት ደመሰሰው። እርሱንም በመስቀል ጠርቆ ከመንገድ አስወግዶታል።>> እንዳለን ቆላ ፪:፲፪-፲፬

ሌሊት በ 10 ሰዓት መጠመቁ ምስጢረ መንግስቱን ለመግለጽ ነው:: በቀን ተጠምቆ ቢሆን ኖሮ መንፈስ ቅዱስ በአምሳለ ርግብ ሲወርድ ሰዎች ይህ መናኛ ርግብ እንጅ መንፈስ ቅዱስ አይደለም ይሉ ነበር::

የተወደዳችሁ ሕዝበ ክርስቲያን:- በየዓመቱ የምናከብረው የጥምቀት በዓል ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ጥምቀት አንዲት ናት አንዳለው (ኤፌ ፬:፭) አባቶችም በሃይማኖት ጸሎት ላይ ወነአምን በአሀቲ ጥምቀት ለሥርየተ ኃጢአት ብለው እንዳስተማሩን ጥምቀት አንዲት የማትደገም የማትከለስ መሆኗን አምነን ከጥምቀት በዓሉም በረከት ለማግኘት ነው:: የአባቶቻችን አምላክ ልዑል እግዚአብሔር በዓሉን የሰላም የፍቅር ያድርግልን:: ከበዓለ ጥምቀቱም በረከት ረድኤት እንዲከፍለን የእናታችን የድንግል ማርያም አማላጅነት አይለየን።

የደብሩ አገልጋይ መምህር በቃሉ ዳዊት

ይእዜኒ ለሰላም ንትልዋ እስመ ተወልደ ክርስቶስ

ይእዜኒ ለሰላም ንትልዋ እስመ ተወልደ ክርስቶስ

በመልአከ ምህረት ቆሞስ አባ ወልደጊዮርጊስ አየለ

ቅዱስ ያሬድ “ይእዜኒ ንትልዋ ለሰላም፤ እንግዲህስ ሰላምን እንከተላት” በማለት ለሰው ልጆች ሁሉ ታላቅ ጥሪ አቅርቧል። ቅዱሱ ይኽን ታላቅ መንፈሳዊ ጥሪ ያቀረበው ለልደት በሚዘመረው ሰላም በተባለው የዚቁ ክፍል ነው። ለሰላም ጥሪ ያቀረበበትንም ምክንያት “እስመ ተወልደ ክርስቶስ ዮም በዛቲ ዕለት ፍሥሐ ንዜኑ ለዘየአምን ዜና ሠናየ ዘውእቱ ሕፃን ኃይሎሙ ወፅንዖሙ ለእስራኤል፤ በዚች ዕለት ክርስቶስ ተወልዷልና ለሚያምኑት ሁሉ ደስታን መልካም የምሥራችንም እናወራለን። ይኽም የተወለደው ሕፃን ለእስራኤል ብርታታቸውና ኀይላቸው ነው” በማለት አብራርቶታል።ቅዱስ ያሬድ ምልጣን በተባለው የዚቁ ክፍልም “ይእዜኒ ለሰላም ንትልዋ፤ መድኃኒነ ተወልደ ነዋ፤ መድኃኒታችን ተወልዷልና አንድም ስለተወለደ እንግዲህስ ሰላምን እንከተላት” ብሏል።

ቅዱስ ያሬድ በሰላሙም ሆነ በምልጣኑ ሰላምን እንከተል ላለው ጥሪው ዐቢይ ምክንያቱ የጌታችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ መወለድ ነው። የጌታችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም መወለድ በዓለሙ ውስጥ ያመጣቸው በርካታና መሠረታዊ ለውጦች አሉ። ከእነዚህም መካከል አንዱ ሰላም ነው።

አዳምና ሔዋን በበደሉበት ወቅት ካጧቸው ጸጋዎች መካከል አንዱ ሰላም ነው። ሰላማቸውን አጥተዋልና አጽናኝና አረጋጊ የሆነውን የተሰበረውን የሚጠግነውን የእግዚአብሔን ድምፅ በገነት መካከል ሲመላለስ በሰሙበት ወቅት ፈሩ። ከእግዚአብሔር ዐይን የማይሸሽጋቸውን ቁጥቋጦ ይሸሸጉበት ዘንድ ተመኙ። ልጃቸው ቃኤንም ወንድሙን ገድሎ ሰላም በራቀው ወቅት ማንም በሌለበት ሀገር ‘’የሚያገኘኝ ሁሉ ይገድለኛል” አለ።

ሰው ሰላሙ የሚሰጠው ከእግዚአብሔር ብቻ ነው። ከእግዚአብሔር በክህደት፣ በኑፋቄና በበደል የተለየ ሰው ሰላም የለውም። በብዙ አዝማድ ቢከበብ፣ ዘመናዊ የጦር መሣርያ የታጠቁ ሠራዊት ቢኖረው፣ ኃያላን በማይበረታቱበት ቅፅር ቢኖር ከእግዚአብሔር ጋር አንድነት የሌለው ሰው ሰላም የለውም። እንዲህ ዓይነቱ ሰው ከውጪ ሲታይ ሰላማዊ መስሎ ቢታይ እንኳ የልብ ሰላም ግን የለውም።

ቅዱሳኑ ግን በነፍስም በሥጋም ኅብረታቸው ከእግዚአብሔር ጋር ስለሆነ ሰዎችን ሁሉ የሚያሸብር መከራ በዓለም በሚከሰትበት ወቅት አይሸበሩም። ታዳጊያቸውና ሰላማቸው እግዚአብሔር የማያንቀላፋ ትጉህ እረኛቸው ከእነርሱ ጋር መሆኑን ስለሚያውቁ ተረጋግተው ይኖራሉ። የእግዚአብሔር ወዳጅ የሆነው ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ “በሞት ጥላ መካከል እንኳ ብሄድ፣ አንተ ከእኔ ጋር ነህና ክፉን አልፈራም፣ በትርህና ምርኩዝህ እነርሱ ያጽናኑኛል” ብሏል። መዝ. ፳፪፣፬። ልጁ ጠቢቡ ሰሎሞንም በተግሣፅ መጽሐፉ “ኃጥእ ማንም ሳያሳድደው ይሸሻል፣ ጻድቅ ግን እንደአንበሳ ተማምኖ ይኖራል” ብሏል። ተግሣጽ ፬፣፩።

ከዚህ እውነታ በመነሣት የአምስት ሺህ አምስት መቶ ዓመታት የሰው ልጆች ኑሮ ምን ይመስል እንደነበር ለመገመት አያስቸግርም። ሰው ከፈጣሪው ርቆ ልጅነቱን አጥቶ ሞት ተፈርዶበት ሰላሙን ተቀምቶ ይኖር ነበር። ጽድቁ እንደ መርገም ጨርቅ ሆኖበት ጉልበቱ ደካማ ጸሎቱ የማይሰማ ነበር። ይኽንን ያጣውን ጸጋና በረከት ደግሞ በራሱ ጥረት ፈጽሞ ሊያመጣው ወይም መልሶ ሊያገኘው አልቻለም ነበር።

ይህን የሰው ልጆችን መከራ በእውነት የተመለከተ እግዚአብሔር የሰላም ባለቤት የሆነውን ልጁን ጌታችን ኢየሱስ ከርስቶስን ወደ ዓለም ሊልከው ወደደ። ለዚህም አስቀድመው ነቢያቱ ትንቢት ተናገሩ። ነቢየ ልዑል ኢሳይያስ “ሕፃን ተውልዶልናልና፣ ወንድ ልጅም ተሰጥቶልናልና፤ አለቅነትም በጫንቃው ላይ ይሆናል።ስሙም ድንቅ መካር ኀያል አምላክ፣ የዘላለም አባት፣ የሰላም አለቃ ተብሎ ይጠራል” በማለት ተናግሯል። ኢሳ. ፱፣፮።

እግዚአብሔር አስቀድሞ ለሥጋዌው የወሰነው ዘመን ደርሶ ያስቆጠረውን ሱባኤና ያናገረውን ትንቢት ሊፈጽም፣ ያስመሰለውንም ምሳሌ እውን ሊያደርግ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷም ነፍስ ነስቶ ያለ ዘርኣ ብእሲ በሕቱም ድንግልና ተጸንሶ በሕቱም ድንግልና በተወለደባት ሌሊት በቤተልሄም ሰማይ ልዩ ምስጋና ያቀረቡት የሰማይ መላእክት “ስብሐት ለእግዚአብሔር በሰማያት ወሰላም በምድር ለዕጓለ እመሕያው ሥምረቱ፤ ክብር ለእግዚአብሔር በሰማያት፣ ሰላምም በምድር፣ ለሰው ልጅም በጎ ፈቃድ ሆነ” በማለት አመስግነዋል። ሉቃ. ፪፣፲፬። መላእክቱ በዚህ ምስጋናቸው ኢሳይያስ የሰላም አለቃ ብሎ የተናገረለት አምላካችን አማኑኤል በእኛ ባሕርይ በመካከላችን በመገኘቱ አጥተነው የነበርነው ሰላማችን ወደ እኛ መምጣቱን አብሥረዋል። እንዲያውም ቅዱስ ሉቃስ እንደጻፈው ከምስጋናቸው አስቀድሞ አንዱ መልአክ በታላቅ ክብርና ግርማ ተገልጦ “ወይቤሎሙ መልአክ ኢትፍርሁ እስመ ናሁ እዜንወክሙ ዐቢየ ዜና ዘይከውን ፍሥሓ ለክሙ ወለኵሉ ዓለም፤እስመ ናሁ ተወልደ ለክሙ ዮም መድኅን ዘውእቱ ክርስቶስ እግዚ ቡሩክ በሀገረ ዳዊት፤ እነሆ ለእናንተና ለሕዝቡ ሁሉ ደስታ የሚሆን ታላቅ የምሥራች እነግራችኋለሁና አትፍሩ፤ እነሆ ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኅን ተወልዶላችኋል፣ ይኸውም ቡሩክ ጌታ ክርስቶስ ነው።

እንግዲህ መልአኩ የተወለደው ጌታ ክርስቶስ መሆኑን የእርሱም የልደቱ ዜና ታላቅ የምሥራች መሆኑን አስረድቶ ሲያበቃ ተከትለውት ከመጡት መላእክት ጋር “ስብሐት ለእግዚአብሔር በሰማያት፣ ወሰላም በምድር ሥምረቱ ለሰብእ” እያለ ወደ ማመስገን ሄደ። ይኽም በጌታችን ልደት የሰው ልጅ ለዘመናት ሲናፍቀው የኖረውን ሰላም ማግኘቱን ያስረዳል። አባታችን ቅዱስ ያሬድም ከመልአኩ በተረዳው መሠረት “ይእዜኒ ለሰላም ንትልዋ፤ እንግዲህስ አንድም አሁንስ ሰላምን እንከተላት ለምን ትለኝ እንደሆነ “መድኀኒነ ተወልደ ነዋ፤ መድኃኒታችን ተወልዷልና” ብሎ ዘመረ።

ቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችን በነቢያትና በሐዋርያት መሠረት ላይ የታነፀች የማዕዘኗ የራስ ድንጋይዋ ደግሞ ክርስቶስ የሆነላት አማናዊት ቤተ ክርስቲያን ናት። በመሆኑም በነቢያት ትንቢት ተነግሮለት የተወለደውን ሐዋርያት በዓለሙ ዙረው ወንጌለ መንግሥቱን የሰበኩለትን ሰማዕታት ስለስሙ ምስክርነት ንጹሕ ደማቸውን ያፈሰሱለትን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ልደት በየዓመቱ በደመቀና በታላቅ መንፈሳዊ ሥነ ሥርዓት ታከብራለች። በዓሉን ማክበር ብቻ ሳይሆን በልደቱ ለሰው ልጆች የተሰጠው ታላቁ አምላካዊ ጸጋ ማለት ሰላም ከልጆቿ ሕይወት እንዳይታጣም አበክራ ታስተምራለች።

ሰላም ለማንኛውም ሰው መንፈሳዊውም ሆነ ምድራዊ ሕይወት መሠረት ነው። የእያንዳንዱ ሰው ሕሊና የሚኖርበትም ዓለም ሰላም ካልሆነ ሠርቶ ማግኘት፣ ወልዶ ማሳደግ፣ ነግዶ ማትረፍ፣ ተረጋግቶ ሃይማኖታዊ ሥርዓትን ፈጽሞ ጽድቅን ማግኘት አይኖርም። በመሆኑም ሰው ከራሱ፣ ከቤተሰቡ አባላት፣ ከጎረቤቶቹ፣ ከመላው የማኅበረሰቡ አባላት፣ ከሥነ ፍጥረት ጋር ሰላም ሊሆን ይገባዋል። ሰላምን ለመጠበቅም ዋጋ መክፈል ይኖርበታል። ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት “ሕስሳ ለሰላም ወዴግና፤ ሰላምን ሻት፣ ተከተላትም” ብሏል። መዝ. ፴፫፣ ፲፬። በሌላ በኩል “መቅደመ ኵሉ ኅሡ ሰላማ ለሀገር፤ ከሁሉ በፊት አስቀድማችሁ የሀገርን ሰላም ሹ” ተብሏል። ይኽ ሁሉ የሚያሳየን ለክርስቲያን ሰላም መሠረታዊና ተቀዳሚ ጉዳይ መኾኑን ነው።

ይሁን እንጂ በአሁኑ ወቅት ሰላም በሀገር፣ በቤተ ክርስቲያን፣ በትዳር፣ በማኅባርዊ ኑሮ እየጠፋ ነው። እያንዳንዱ ግለሰብ ውስጣዊ ሰላም አጥቶ ለጭንቀትና ለአእምሮ ሕመም በመዳረግ ላይ ይገኛል። ምንም እንኳን በዚህ በውጪው ዓለም ቁሳዊው ፍላጎታችን በአንጻራዊነት ሊሟላልን በሚችልበት ዓለም ብንኖርም ካጌጠው ፊታችንና ልብሳችን ጀርባ ያለው ሕሊናችን ግን ሰላምን ፍለጋ ላይ ነው። ለዚህ ደግሞ ዋና መፍትሄው ሰላማችን ወደ ሆነው ወደ ጌታችንና ወደ አምላካችን ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ በጎ ፈቃዱን በመፈጸም መቅረብ ነው።

የጌታችንን ልደት በምናስብበት ወቅት ራሳችን ከራሳችንና ከሌሎች ጋር ሰላማውያን መሆናችንን መመርመር ያስፈልጋል። በነገር፣ በጥልና በክርክር ተይዞ የጌታችንን ልደት ማክበር ከመሠረታዊ አስተምህሮ ውጪ መሆን ነው፤ በረከትም አያስገኝም። ከዚኽም ጋር ሰላማችንን ያገኘንበትን የጌታችንን ልደት ስናከብር ሰላማቸው በዲያብሎስና በዚኽ ዓለም ጉልበተኞች ተናግቶባቸው ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው በስደት ያሉትን፣ ታምመው ሰላም አጥተው በየጤና ተቋማቱ የሚንከራተቱትን በማሰብና ሰላማዊው ኢየሱስ ክርስቶስ የረድኤት እጁን እንዲዘረጋላቸው አጥብቀን በመጸለይ ጭምር መሆን አለበት።

ካህናት በቤተ መቅደስ በቅዳሴ ወቅት ዘወትር “ሰላም ለኵልክሙ፤ ሰላም ለሁላችሁ ይኹን” ሲሉን “ከመንፈስህ ጋራ” ብሎ በመመለስ ብቻ ሰላም አይገኝም። ራስን ለክርስቶስ ቃል አስገዝቶ በወንጌል ቃል ተመርቶ በምክረ ካህንና በፈቃደ ካህን ሕይወትን መምራትና ንስሐ ገብቶ በቅዱስ ቁርባን መወሰንን ጭምር ገንዘብ ማድረግ ያስፈልጋል። እስካሁን የነበረውን ጊዜያችንን ከእግዚአብሔር ፈቃድ በራቀ መንገድ ስንመራ ቆይተናል። አሁን ግን ወደ ነፍሳችን እረኛና ሰላማችን ወደሆነው ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ በንስሐ መልሰን በፍቅርና በአንድነት በአንዲት ቤተ ክርስቲያናችን ከሽንገላ በራቀ ከንፈራችን ንጹሕ ምስጋናን ልናቀርብለት ይገባናል። ያለበለዚያ በጥላቻ፣ በሐሜትና በተንኮል ሆነን የምናቀርበውን መሥዋዕት፣ የምንቀበለውን ቁርባን፣ የምናመሰግነውን ምስጋና በአጠቃላይ ማንኛውንም መንፈሳዊ አገልግሎታችንን የቃኤልን መሥዋዕት እንደተጸየፈ ይጸየፍብናል።

ቅዱስ ጳውሎስ “የጨለማን ሥራ ከእኛ እናርቅ” እንዳለው እኛም እግዚአብሔር የማይወደውን የጥልና የክርክር ኑሯችንን ትተን የሰላሙን መንገድ እንከተል። ምክንያቱም “መድኃኒነ ተወልደ ነዋ፤ መድኃኒታችን ተወልዷልና”። ይኽ በቤተልሄም በከብቶች ግርግም በጨርቅ ተጠቅልሎ እንስሳት እስትንፋሻቸውን የገበሩለት መድኃኒታችን የሰላም ባለቤት ነው። ከእኛ ሰላምን ይሻል። ከዚኽም በላይ “አሁን ግን ቀድሞ ርቃችሁ የነበራችሁ እናንተ በኢየሱስ ክርስቶስ ሆናችሁ በክርስቶስ ደም ቀረባችሁ። ሁለቱን አንድ ያደረገ ሰላማችን እርሱ ነውና፣ በሥጋውም በመካከል የነበረውን የጥል ግድግዳ አፍርሶ ጥልን ሻረ። ሁለቱንም አድሶ አንድ ያደርጋቸው ዘንድ በሥርዓቱ የትእዛዝን ሕግ አጠፋ፤ ዕርቅንም አደረገ። በመስቀሉም በአንድ ሥጋው ሁለቱን ወደ እግዚአብሔር አቀረባቸው፤ በእርሱም ጥልን አጠፋ። መጥቶም ቀርበን ለነበርነው ሰላምን ርቃችሁ ለነበራችሁት ለእናንተም ሰላምን ሰጠ” ተብሏል።

በመሆኑም ሰላማችን የተወለደበትን ዕለት ስናከብር የእርሱ መሆናችንንም በምናስብበት ወቅት ሁሉ የሰላም ልጆች መሆናችንን ልናስብና የሰላም ጸር ከሆኑ ድርጊቶች ልንርቅ ያስፈልጋል። ዘወትርም ለእርሱ የምትገዛ ሀገራችንን እግዚአብሔር በምሕረቱ አስቦ ሰላሟን ይጠብቅላት ዘንድ አጥብቀን መጸለይ ይጠበቅብናል። እግዚአብሔር ሰላሙን ለእኛና ለሀገራችን እንዲሁም ለመላው የዓለም ሕዝብ ያድልልን። አሜን።