ይእዜኒ ለሰላም ንትልዋ እስመ ተወልደ ክርስቶስ

ይእዜኒ ለሰላም ንትልዋ እስመ ተወልደ ክርስቶስ

በመልአከ ምህረት ቆሞስ አባ ወልደጊዮርጊስ አየለ

ቅዱስ ያሬድ “ይእዜኒ ንትልዋ ለሰላም፤ እንግዲህስ ሰላምን እንከተላት” በማለት ለሰው ልጆች ሁሉ ታላቅ ጥሪ አቅርቧል። ቅዱሱ ይኽን ታላቅ መንፈሳዊ ጥሪ ያቀረበው ለልደት በሚዘመረው ሰላም በተባለው የዚቁ ክፍል ነው። ለሰላም ጥሪ ያቀረበበትንም ምክንያት “እስመ ተወልደ ክርስቶስ ዮም በዛቲ ዕለት ፍሥሐ ንዜኑ ለዘየአምን ዜና ሠናየ ዘውእቱ ሕፃን ኃይሎሙ ወፅንዖሙ ለእስራኤል፤ በዚች ዕለት ክርስቶስ ተወልዷልና ለሚያምኑት ሁሉ ደስታን መልካም የምሥራችንም እናወራለን። ይኽም የተወለደው ሕፃን ለእስራኤል ብርታታቸውና ኀይላቸው ነው” በማለት አብራርቶታል።ቅዱስ ያሬድ ምልጣን በተባለው የዚቁ ክፍልም “ይእዜኒ ለሰላም ንትልዋ፤ መድኃኒነ ተወልደ ነዋ፤ መድኃኒታችን ተወልዷልና አንድም ስለተወለደ እንግዲህስ ሰላምን እንከተላት” ብሏል።

ቅዱስ ያሬድ በሰላሙም ሆነ በምልጣኑ ሰላምን እንከተል ላለው ጥሪው ዐቢይ ምክንያቱ የጌታችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ መወለድ ነው። የጌታችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም መወለድ በዓለሙ ውስጥ ያመጣቸው በርካታና መሠረታዊ ለውጦች አሉ። ከእነዚህም መካከል አንዱ ሰላም ነው።

አዳምና ሔዋን በበደሉበት ወቅት ካጧቸው ጸጋዎች መካከል አንዱ ሰላም ነው። ሰላማቸውን አጥተዋልና አጽናኝና አረጋጊ የሆነውን የተሰበረውን የሚጠግነውን የእግዚአብሔን ድምፅ በገነት መካከል ሲመላለስ በሰሙበት ወቅት ፈሩ። ከእግዚአብሔር ዐይን የማይሸሽጋቸውን ቁጥቋጦ ይሸሸጉበት ዘንድ ተመኙ። ልጃቸው ቃኤንም ወንድሙን ገድሎ ሰላም በራቀው ወቅት ማንም በሌለበት ሀገር ‘’የሚያገኘኝ ሁሉ ይገድለኛል” አለ።

ሰው ሰላሙ የሚሰጠው ከእግዚአብሔር ብቻ ነው። ከእግዚአብሔር በክህደት፣ በኑፋቄና በበደል የተለየ ሰው ሰላም የለውም። በብዙ አዝማድ ቢከበብ፣ ዘመናዊ የጦር መሣርያ የታጠቁ ሠራዊት ቢኖረው፣ ኃያላን በማይበረታቱበት ቅፅር ቢኖር ከእግዚአብሔር ጋር አንድነት የሌለው ሰው ሰላም የለውም። እንዲህ ዓይነቱ ሰው ከውጪ ሲታይ ሰላማዊ መስሎ ቢታይ እንኳ የልብ ሰላም ግን የለውም።

ቅዱሳኑ ግን በነፍስም በሥጋም ኅብረታቸው ከእግዚአብሔር ጋር ስለሆነ ሰዎችን ሁሉ የሚያሸብር መከራ በዓለም በሚከሰትበት ወቅት አይሸበሩም። ታዳጊያቸውና ሰላማቸው እግዚአብሔር የማያንቀላፋ ትጉህ እረኛቸው ከእነርሱ ጋር መሆኑን ስለሚያውቁ ተረጋግተው ይኖራሉ። የእግዚአብሔር ወዳጅ የሆነው ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ “በሞት ጥላ መካከል እንኳ ብሄድ፣ አንተ ከእኔ ጋር ነህና ክፉን አልፈራም፣ በትርህና ምርኩዝህ እነርሱ ያጽናኑኛል” ብሏል። መዝ. ፳፪፣፬። ልጁ ጠቢቡ ሰሎሞንም በተግሣፅ መጽሐፉ “ኃጥእ ማንም ሳያሳድደው ይሸሻል፣ ጻድቅ ግን እንደአንበሳ ተማምኖ ይኖራል” ብሏል። ተግሣጽ ፬፣፩።

ከዚህ እውነታ በመነሣት የአምስት ሺህ አምስት መቶ ዓመታት የሰው ልጆች ኑሮ ምን ይመስል እንደነበር ለመገመት አያስቸግርም። ሰው ከፈጣሪው ርቆ ልጅነቱን አጥቶ ሞት ተፈርዶበት ሰላሙን ተቀምቶ ይኖር ነበር። ጽድቁ እንደ መርገም ጨርቅ ሆኖበት ጉልበቱ ደካማ ጸሎቱ የማይሰማ ነበር። ይኽንን ያጣውን ጸጋና በረከት ደግሞ በራሱ ጥረት ፈጽሞ ሊያመጣው ወይም መልሶ ሊያገኘው አልቻለም ነበር።

ይህን የሰው ልጆችን መከራ በእውነት የተመለከተ እግዚአብሔር የሰላም ባለቤት የሆነውን ልጁን ጌታችን ኢየሱስ ከርስቶስን ወደ ዓለም ሊልከው ወደደ። ለዚህም አስቀድመው ነቢያቱ ትንቢት ተናገሩ። ነቢየ ልዑል ኢሳይያስ “ሕፃን ተውልዶልናልና፣ ወንድ ልጅም ተሰጥቶልናልና፤ አለቅነትም በጫንቃው ላይ ይሆናል።ስሙም ድንቅ መካር ኀያል አምላክ፣ የዘላለም አባት፣ የሰላም አለቃ ተብሎ ይጠራል” በማለት ተናግሯል። ኢሳ. ፱፣፮።

እግዚአብሔር አስቀድሞ ለሥጋዌው የወሰነው ዘመን ደርሶ ያስቆጠረውን ሱባኤና ያናገረውን ትንቢት ሊፈጽም፣ ያስመሰለውንም ምሳሌ እውን ሊያደርግ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷም ነፍስ ነስቶ ያለ ዘርኣ ብእሲ በሕቱም ድንግልና ተጸንሶ በሕቱም ድንግልና በተወለደባት ሌሊት በቤተልሄም ሰማይ ልዩ ምስጋና ያቀረቡት የሰማይ መላእክት “ስብሐት ለእግዚአብሔር በሰማያት ወሰላም በምድር ለዕጓለ እመሕያው ሥምረቱ፤ ክብር ለእግዚአብሔር በሰማያት፣ ሰላምም በምድር፣ ለሰው ልጅም በጎ ፈቃድ ሆነ” በማለት አመስግነዋል። ሉቃ. ፪፣፲፬። መላእክቱ በዚህ ምስጋናቸው ኢሳይያስ የሰላም አለቃ ብሎ የተናገረለት አምላካችን አማኑኤል በእኛ ባሕርይ በመካከላችን በመገኘቱ አጥተነው የነበርነው ሰላማችን ወደ እኛ መምጣቱን አብሥረዋል። እንዲያውም ቅዱስ ሉቃስ እንደጻፈው ከምስጋናቸው አስቀድሞ አንዱ መልአክ በታላቅ ክብርና ግርማ ተገልጦ “ወይቤሎሙ መልአክ ኢትፍርሁ እስመ ናሁ እዜንወክሙ ዐቢየ ዜና ዘይከውን ፍሥሓ ለክሙ ወለኵሉ ዓለም፤እስመ ናሁ ተወልደ ለክሙ ዮም መድኅን ዘውእቱ ክርስቶስ እግዚ ቡሩክ በሀገረ ዳዊት፤ እነሆ ለእናንተና ለሕዝቡ ሁሉ ደስታ የሚሆን ታላቅ የምሥራች እነግራችኋለሁና አትፍሩ፤ እነሆ ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኅን ተወልዶላችኋል፣ ይኸውም ቡሩክ ጌታ ክርስቶስ ነው።

እንግዲህ መልአኩ የተወለደው ጌታ ክርስቶስ መሆኑን የእርሱም የልደቱ ዜና ታላቅ የምሥራች መሆኑን አስረድቶ ሲያበቃ ተከትለውት ከመጡት መላእክት ጋር “ስብሐት ለእግዚአብሔር በሰማያት፣ ወሰላም በምድር ሥምረቱ ለሰብእ” እያለ ወደ ማመስገን ሄደ። ይኽም በጌታችን ልደት የሰው ልጅ ለዘመናት ሲናፍቀው የኖረውን ሰላም ማግኘቱን ያስረዳል። አባታችን ቅዱስ ያሬድም ከመልአኩ በተረዳው መሠረት “ይእዜኒ ለሰላም ንትልዋ፤ እንግዲህስ አንድም አሁንስ ሰላምን እንከተላት ለምን ትለኝ እንደሆነ “መድኀኒነ ተወልደ ነዋ፤ መድኃኒታችን ተወልዷልና” ብሎ ዘመረ።

ቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችን በነቢያትና በሐዋርያት መሠረት ላይ የታነፀች የማዕዘኗ የራስ ድንጋይዋ ደግሞ ክርስቶስ የሆነላት አማናዊት ቤተ ክርስቲያን ናት። በመሆኑም በነቢያት ትንቢት ተነግሮለት የተወለደውን ሐዋርያት በዓለሙ ዙረው ወንጌለ መንግሥቱን የሰበኩለትን ሰማዕታት ስለስሙ ምስክርነት ንጹሕ ደማቸውን ያፈሰሱለትን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ልደት በየዓመቱ በደመቀና በታላቅ መንፈሳዊ ሥነ ሥርዓት ታከብራለች። በዓሉን ማክበር ብቻ ሳይሆን በልደቱ ለሰው ልጆች የተሰጠው ታላቁ አምላካዊ ጸጋ ማለት ሰላም ከልጆቿ ሕይወት እንዳይታጣም አበክራ ታስተምራለች።

ሰላም ለማንኛውም ሰው መንፈሳዊውም ሆነ ምድራዊ ሕይወት መሠረት ነው። የእያንዳንዱ ሰው ሕሊና የሚኖርበትም ዓለም ሰላም ካልሆነ ሠርቶ ማግኘት፣ ወልዶ ማሳደግ፣ ነግዶ ማትረፍ፣ ተረጋግቶ ሃይማኖታዊ ሥርዓትን ፈጽሞ ጽድቅን ማግኘት አይኖርም። በመሆኑም ሰው ከራሱ፣ ከቤተሰቡ አባላት፣ ከጎረቤቶቹ፣ ከመላው የማኅበረሰቡ አባላት፣ ከሥነ ፍጥረት ጋር ሰላም ሊሆን ይገባዋል። ሰላምን ለመጠበቅም ዋጋ መክፈል ይኖርበታል። ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት “ሕስሳ ለሰላም ወዴግና፤ ሰላምን ሻት፣ ተከተላትም” ብሏል። መዝ. ፴፫፣ ፲፬። በሌላ በኩል “መቅደመ ኵሉ ኅሡ ሰላማ ለሀገር፤ ከሁሉ በፊት አስቀድማችሁ የሀገርን ሰላም ሹ” ተብሏል። ይኽ ሁሉ የሚያሳየን ለክርስቲያን ሰላም መሠረታዊና ተቀዳሚ ጉዳይ መኾኑን ነው።

ይሁን እንጂ በአሁኑ ወቅት ሰላም በሀገር፣ በቤተ ክርስቲያን፣ በትዳር፣ በማኅባርዊ ኑሮ እየጠፋ ነው። እያንዳንዱ ግለሰብ ውስጣዊ ሰላም አጥቶ ለጭንቀትና ለአእምሮ ሕመም በመዳረግ ላይ ይገኛል። ምንም እንኳን በዚህ በውጪው ዓለም ቁሳዊው ፍላጎታችን በአንጻራዊነት ሊሟላልን በሚችልበት ዓለም ብንኖርም ካጌጠው ፊታችንና ልብሳችን ጀርባ ያለው ሕሊናችን ግን ሰላምን ፍለጋ ላይ ነው። ለዚህ ደግሞ ዋና መፍትሄው ሰላማችን ወደ ሆነው ወደ ጌታችንና ወደ አምላካችን ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ በጎ ፈቃዱን በመፈጸም መቅረብ ነው።

የጌታችንን ልደት በምናስብበት ወቅት ራሳችን ከራሳችንና ከሌሎች ጋር ሰላማውያን መሆናችንን መመርመር ያስፈልጋል። በነገር፣ በጥልና በክርክር ተይዞ የጌታችንን ልደት ማክበር ከመሠረታዊ አስተምህሮ ውጪ መሆን ነው፤ በረከትም አያስገኝም። ከዚኽም ጋር ሰላማችንን ያገኘንበትን የጌታችንን ልደት ስናከብር ሰላማቸው በዲያብሎስና በዚኽ ዓለም ጉልበተኞች ተናግቶባቸው ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው በስደት ያሉትን፣ ታምመው ሰላም አጥተው በየጤና ተቋማቱ የሚንከራተቱትን በማሰብና ሰላማዊው ኢየሱስ ክርስቶስ የረድኤት እጁን እንዲዘረጋላቸው አጥብቀን በመጸለይ ጭምር መሆን አለበት።

ካህናት በቤተ መቅደስ በቅዳሴ ወቅት ዘወትር “ሰላም ለኵልክሙ፤ ሰላም ለሁላችሁ ይኹን” ሲሉን “ከመንፈስህ ጋራ” ብሎ በመመለስ ብቻ ሰላም አይገኝም። ራስን ለክርስቶስ ቃል አስገዝቶ በወንጌል ቃል ተመርቶ በምክረ ካህንና በፈቃደ ካህን ሕይወትን መምራትና ንስሐ ገብቶ በቅዱስ ቁርባን መወሰንን ጭምር ገንዘብ ማድረግ ያስፈልጋል። እስካሁን የነበረውን ጊዜያችንን ከእግዚአብሔር ፈቃድ በራቀ መንገድ ስንመራ ቆይተናል። አሁን ግን ወደ ነፍሳችን እረኛና ሰላማችን ወደሆነው ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ በንስሐ መልሰን በፍቅርና በአንድነት በአንዲት ቤተ ክርስቲያናችን ከሽንገላ በራቀ ከንፈራችን ንጹሕ ምስጋናን ልናቀርብለት ይገባናል። ያለበለዚያ በጥላቻ፣ በሐሜትና በተንኮል ሆነን የምናቀርበውን መሥዋዕት፣ የምንቀበለውን ቁርባን፣ የምናመሰግነውን ምስጋና በአጠቃላይ ማንኛውንም መንፈሳዊ አገልግሎታችንን የቃኤልን መሥዋዕት እንደተጸየፈ ይጸየፍብናል።

ቅዱስ ጳውሎስ “የጨለማን ሥራ ከእኛ እናርቅ” እንዳለው እኛም እግዚአብሔር የማይወደውን የጥልና የክርክር ኑሯችንን ትተን የሰላሙን መንገድ እንከተል። ምክንያቱም “መድኃኒነ ተወልደ ነዋ፤ መድኃኒታችን ተወልዷልና”። ይኽ በቤተልሄም በከብቶች ግርግም በጨርቅ ተጠቅልሎ እንስሳት እስትንፋሻቸውን የገበሩለት መድኃኒታችን የሰላም ባለቤት ነው። ከእኛ ሰላምን ይሻል። ከዚኽም በላይ “አሁን ግን ቀድሞ ርቃችሁ የነበራችሁ እናንተ በኢየሱስ ክርስቶስ ሆናችሁ በክርስቶስ ደም ቀረባችሁ። ሁለቱን አንድ ያደረገ ሰላማችን እርሱ ነውና፣ በሥጋውም በመካከል የነበረውን የጥል ግድግዳ አፍርሶ ጥልን ሻረ። ሁለቱንም አድሶ አንድ ያደርጋቸው ዘንድ በሥርዓቱ የትእዛዝን ሕግ አጠፋ፤ ዕርቅንም አደረገ። በመስቀሉም በአንድ ሥጋው ሁለቱን ወደ እግዚአብሔር አቀረባቸው፤ በእርሱም ጥልን አጠፋ። መጥቶም ቀርበን ለነበርነው ሰላምን ርቃችሁ ለነበራችሁት ለእናንተም ሰላምን ሰጠ” ተብሏል።

በመሆኑም ሰላማችን የተወለደበትን ዕለት ስናከብር የእርሱ መሆናችንንም በምናስብበት ወቅት ሁሉ የሰላም ልጆች መሆናችንን ልናስብና የሰላም ጸር ከሆኑ ድርጊቶች ልንርቅ ያስፈልጋል። ዘወትርም ለእርሱ የምትገዛ ሀገራችንን እግዚአብሔር በምሕረቱ አስቦ ሰላሟን ይጠብቅላት ዘንድ አጥብቀን መጸለይ ይጠበቅብናል። እግዚአብሔር ሰላሙን ለእኛና ለሀገራችን እንዲሁም ለመላው የዓለም ሕዝብ ያድልልን። አሜን።