ደብረ ዘይት
ደብረ ዘይት
በመጋቤ ሐዲስ ፍቅረ ማርያም ባዘዘው
በቦሌ መንበረ ብርሃን ቅዱስ እግዚአብሔር አብ ቤተክርስቲያን የሐዲስ ኪዳን የትርጓሜ መምህር
የዐቢይ ጾም አምስተኛ ሳምንት ደብረ ዘይት በመባል ይጠራል በዚህ ቀን ጌታችንና መድኃኒታች ኢየሱስ ክርስቶስ ስለዓለም ፍጻሜ ወይንም የመጨረሻው የፍርድ ቀን ምን እንደሚመስል ያስተማረበት ቀን ነው፡፡ ይህም ቀን ደብረ ዘይት በመባል ይታወቃል፡፡ ደብር ማለት ተራራ ሲሆን ዘይት ማለት ደግሞ ወይራ ማለት ነው፡፡ ይህም ማለት ወይራ የበዛበት ተራራ ማለት ነው፡፡ ለዛሬው ርእስ የሚሆነን ድንጋይ በድንጋይ ላይ ሳይፈርስ አይቀርም በሚል ይሆናል፡፡
‹‹አማን እብለክሙ ኢይትኃደግ ዝየ ዕብን ዲበ ዕብን ዘኢይትነሠት››
እውነት እነግራችኋለሁ ድንጋይ በድንጋይ ላይ ሳፈርስ አይቀርም ማቴ. 24፤2
ቃሉም እንዲህ ሲል ይገልጻል፤- ኢየሱስም ከመቅደስ ወጥቶ ሄደ፥ ደቀ መዛሙርቱም የመቅደሱን ግንቦች ሊያሳዩት ቀረቡ። እርሱ ግን መልሶ፦ ይህን ሁሉ ታያላችሁን? እውነት እላችኋለሁ፥ ድንጋይ በድንጋይ ላይ ሳይፈርስ በዚህ አይቀርም አላቸው። እንደግዲህ ከዚህ ገጸ ንባብ የምንመለከተው ስለ አንድ የመቅደስ ድንጋይ የፀሐይ ብርሃን አርፎበት ዐይንን የሚስብና የሚያምር ሆኖ የተመለከቱት ደቀ መዛሙርቱ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስን ድንጋዩን እንዲመለከተው ጋበዙት፡፡ እርሱ ግን ሁሉን የሚያውቅ፤ የሁሉ አስገኝ መሆኑን የዘነጉት ይመስላሉ፡፡ ለመሆኑ ነገሩ የምጻት ነገር ከሆነ ዘንድ ስለመቅደሱ ድንጋይ ለምን ሊነሣ ቻለ? የመቅደሱ ድንጋይ ምንድን ነው፡፡
እንግዲህ የመቅደሱን ድንጋይ ስንመለከት በቁሙ የሰው እጅ የሠራው ሥራ ሁሉ በአዲስ ይሠራል ይተካል በተሻሻለ ሁኔታ ወቅቱ በሚጠብቀው አይነት ሊሠራ ይችላል፡፡ ከዚህ ጋር ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እየተናገረ ያለው ሰው ሰለተባለ መቅደስ ነበር፡፡
ሐዋርያት የፀሐይ ብርሃን ሰፍሮበት አምሮ ለዐይን የሚስብ ሆኖ በተመለከቱት ጊዜ ነበር ጌታችንን ተመለከተው ያሉት፡፡ ስለዚህ መቅደሱ ማን ነው ስንል፡፡
መቅደስ ሰው፡- የመጀመሪያው መቅደስ የእግዚአብሔር ማደሪያ በራሱ አርአያና ምሳሌ የፈጠረው ሰው የተባለው ክቡር ፍጥረት ነው፡፡ የፀሐይ ብርሃን ሰፍሮበት መታየቱ ዕድሜ ነው፡፡ ዕድሜ ፀሐይ ነው፡፡ ደምቆ ይታያል ሁሉንም የምንሠራበት ጊዜ ነው፡፡ ነገር ግን ፀሐይ እንደወጣ አይኖርም ይመሻል ይነጋል በመሆኑን ዕድሜም እንዲሁ ነው፡፡ የሰው ልጅ ይወለዳል፡፡ የፀሐይ ብርሃን የተባለ ውበት፤ ደም ግባት መቅደስ በተባለው ሰውነት ላይ ደምቆ ይታያል እንዲህ እንደሆነ ግን አይኖርም በጊዜው ያልፋል፡፡ ለዚህም መጽሐፈ መክብብ እንዲህ ይላል፡፡
መክ.12-1 የጭንቀት ቀን ሳይመጣ በጕብዝናህ ወራት ፈጣሪህን አስብ ደስ አያሰኙም የምትላቸውም ዓመታት ሳይደርሱ ፀሐይና ብርሃን ጨረቃና ከዋክብትም ሳይጨልሙ፥ ደመናትም ከዝናብ በኋላ ሳይመለሱ ቤት ጠባቆች በሚንቀጠቀጡበት፥ ኃያላን ሰዎችም በሚጎብጡበት፥ ጥቂቶች ሆነዋልና ፈጭታዎች ሥራ በሚፈቱበት፥ በመስኮትም ሆነው የሚመለከቱ በሚጨልሙበት፥ በአደባባይም ደጆቹ በሚዘጉበት ቀን የወፍጮ ድምፅ ሲላሽ፥ ከወፍ ድምፅ የተነሣ ሰው ሲነሣ፥ ዜማም የሚጮኹ ሴቶች ልጆች ሁሉ ዝግ ሲሉ ከፍ ያለውን ደግሞ ሲፈሩ፥ ድንጋጤም በመንገድ ላይ ሲሆን ለውዝም ሲያብብ፥ አንበጣም እንደ ሸክም ሲከብድ፥ ፈቃድም ሲጠፋ ሰው ወደ ዘላለም ቤት ሲሄድ፥ አልቃሾችም በአደባባይ ሲዞሩ የብር ድሪ ሳይበጠስ፥ የወርቅም ኵስኵስት ሳይሰበር፥ ማድጋውም በምንጭ አጠገብ ሳይከሰከስ፥ መንኰራኵሩም በጕድጓድ ላይ ሳይሰበር፥ አፈርም ወደ ነበረበት ምድር ሳይመለስ፥ ነፍስም ወደ ሰጠው ወደ እግዚአብሔር ሳይመለስ ፈጣሪህን አስብ። ይህ ሁሉ የሚነግረን ዕድሜ የተባለ የፀሐይ ብርሃን ሳይጠልቅ ሰው በዚህ ዓለም ምን መሥራት እንዳለበት የሚገልጽ ነው፡፡ ምንም ማማር፤ ውበት ቢኖርም ቅሉ ሁሉን እንዳልነበረ የሚያደርግ የማይለይ ድኀ ባዕለ ጸጋ የማይል ሞት የተባለ ትልቅ ነገርን ተሸክመን ነው የምንኖረው፡፡ ጌታችንም ድንጋይ በድንጋይ ላይ ሳይፈርስ አይቀርም ሲል እንግዲህ ሰው የተባለው መቅደስ ሞቱ አይቀርምና በጎ ሥራ መሥራት እንደለብን የሚገልጽ ነው፡፡ ሰው የሚሞት ከሆነ ለጥቂትም ጊዜ ቢሆን በጎ ሥራ መሥራት ይኖርበታል፡፡ ሥም አይሞትም በጎ ሥራን መቃብር አይሸፍነውም፡፡ የተፈጠርንበት ለበጎ ዓላማ ከሆነ በጎ ሥራ መሥራትን ገንዘብ ማድረግ ራስን ለታላቅ ክብር ማብቃት ነው፡፡
መቅደስ፡- ድንጋይ በድንጋይ ላይ ሳይፈርስ አይቀርም ሲል ሌላው ምሥጢር ይህ መቅደስ በብሉይ ኪዳን የነበረ መቅደስ ነው፡፡ ነገር ግን በሐዲስ ኪዳን እውነተኛዋ ቤተመቅደስ በክርስቶስ ደም ስለምትታነጸው መቅደስ እየተናገረ ነበር ምክንያቱም የብሉይ ኪዳን መቅደስ የበግ መስዋዕት ቢቀርብባትም ቅሉ ሰው ሊድንበት አልቻለም፡፡ አሁን ግን አማናዊው በግ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱን ቤዛ አድርጎ ከነበረብን የሞት ፍዳ ነጻ አድርጎ ቀራንዮ ላይ መቅደሱን አንጾልናል፡፡ እንዲህ ሲል ስለሐዲስ ኪዳን መቅደስ መሠራት እየነገርን ነበር፡፡
መቅደስ፡- ሌላው ነገር ደግሞ ድንጋይ በድንጋ ላይ ሳይፈርስ አይቀርም ሲባል የሰው ልጆችን የመዳን ምሥጢር የሚናገር ማንነት ያለው ምዕራፍ ነው፡፡ ይህ ሲባል እንደሚታወቀው አዳም ከ 7 ዓመት በኋላ በጥፋቱ ከገነት ተባርሮ ወጥቷል በመሆኑም ባሕርዩ ጎስቋላ ሆኗል፡፡ በአጠቃላይ አዳም የተባለ መቅደስ ሰውነት በኃጢአት ምክንያት ማንነቱን አጥቷል ጌታችን ይህን የተበላሸ ባሕርይ ወይንም ማንነት እንደገና ሊሠራው ሰው ሆኗልና ለዚህ ነበር ድንጋይ በድንጋይ ሳርፈርስ አይቀርም በማለት አዳም የተባለ መቅደስ በኃጢአት ምክንያት ቢፈርስም ዳግመኛ እርሱ ሰው በመሆን አዳም መቅደስን ሠርቶታል ወይንም አንፆታል፡፡ ከዚህ በኋላ ግን ይህ መቅደስ ራሱን ካልጠበቀ ክርስቶስ ዳግመኛ አይሞትለትም፡፡ እርሱ የሚመጣው ይህን ዓለም ለማሳለፍ እንጅ፡፡ ይልቁንም ሰው ራሱን ከኃጢአት ለይቶ በንስሐ በሥጋ ወደሙ ታትሞ ሊኖር ግድ ነው፡፡ በዚሁ ምዕራፍ ቁጥር 19 ላይ እንዲህ ይላል፡- በዚያችም ወራት ለርጉዞችና ለሚያጠቡ ወዮላቸው። ርጉዝና የሚያጠቡ የተባሉ በኃጢአት ውስጥ ያሉ ንስሐ ያልገቡ ኃጢአትን እየሠሩ ምንም ለማይመስላቸው ሰዎች በንስሐ ተዘጋጅተው እንዲኖሩ የተላለፈ ቃል ነው፡፡ እንደሚታወቀው ይህን መቅደስ ለመሥራት የጨረሰባቸው ጊዜ 46 ዓመት ነው ይህ ቁጥር በዕብራይስጥ ራሱን የቻለ አቆጣጠር አለው 46 ሊል የአዳምን ማንነት የያዘ ቁጥር ነው፡፡ ADAM( አዳም) የሚለው በቁጥር ሲያስቀምጡት A አልፋ አንድ ቁጥር ነው D ዴልታ አራት ቁጥር ነው A አልፍ አንድ M May አርባ ነው በአጠቃላይ 46 ይሞላል ማለት ነው፡፡ ይህም ማለት ደግሞ መቅደስ የተባለ አዳም መሆኑን ይገልጻል ማለት ነው፡፡ በአጠቃላይ ኢየሱስ ክርስቶስ በሞቱ አዳም የተባለ መቅደስን ዳግመኛ እንደሠራው የሚናገር ነው፡፡
ይቀጥላል …ይቆየን
