በዓለ ጥምቀት

በዓለ ጥምቀት

 

ጥምቀት አጥመቀ አጠመቀ (ነከረ) ከሚለው የግዕዝ ቃል የወጣ ሲሆን ትርጉሙም መጠመቅ መነከር ማለት ነው:: በዚህም ምስጢር ከእግዚአብሔር በመንፈስ እንወለዳለን ::

የጥምቀት ምሳሌ በብሉይ ኪዳን ተጠቅሶ ይገኛል::

  1. የሕዝበ እስራኤል ቀይ ባሕርን መሻገር:: <<ሁሉም በባህር መካከል ተሻገሩ ሁሉም ሙሴን ይተባበሩ ዘንድ በደመናና በባህር ተጠመቁ>> 1 ቆሮ 10:2 ዘጸ 14:22
  2. ኖህና ቤተሰቡ በእምነት መርከብ ሰርተው ከጥፋት ውኃ መዳናቸው 1 ጴጥ 3: 20-21
  3. በኢያሱ የምስፍንና ዘመን የእግዚአብሔርን የቃል ኪዳን ታቦት የተሸከሙት የካህናት እግሮች በውሃ ዳር ሲጠልቁ ከላይ የሚወርደው ውሃ ቆሞ እስራኤል ዮርዳኖስን በደረቅ መሻገራቸው 2 ኢያ 3፡15

ከዚህ ቀጥለን የወልድን ጥምቀት (ጥምቀተ ወልድ) እናያለን

ጌታችን ከእመቤታችን በኅቱም ድንግልና ተጸንሶ በኅቱም ድንግልና ተወለደ:: በተወለደ በ 40 ቀኑ ዕጉለ ርግብ ዘውገ መዕነቅ ይዞ ቤተ እግዚአብሔር በመግባት በመውጣት ሕገ መጽሐፋዊን ሕገ ጠባዕያዊን ሲፈጽም ‘በበህቅ ልህቀ እንዘ ይትኤዘዝ ለአዝማዲሁ እንተ ይእቲ እሙ’ እንዲል (ሉቃ 2:51):: ለእናቱ እየታዘዘ አድጎ 30 ዓመት ሲሞላው ወደ ዮርዳኖስ ሄደ:: ዕለቱ ማክሰኞ ሰዓቱ 10 ሰዓት ሌሊት ነው:: ዮሐንስን አጥምቀኝ አለው:: ዮሐንስም ጌታዬ እኔ ባንተ ልጠመቅ ይገባኛል እንጅ አንተ በእኔ አንዴት ትጠመቃለህ አለው::ጌታም መልሶ ሕግን ሁሉ ልንፈጽም ይገባናልና አለው:: አንድም ጥምቀት አንዲት መሆኗን ያመለክታል::

ዮሐንስም መልሶ ሌላውን በአንተ ስም አጠምቃለሁ አንተን በማን ስም ላጥምቅህ አለው:: ጌታችንም እንዲህ አለው ‘ወልዱ ለቡሩክ ከሣቴ ብርሃን ተሣሃለነ’ እያልክ አጥምቀኝ አለው:: ዮሐንስም እሺ አለ:: ጌታችንም ሊጠመቅ ከዮርዳኖስ ባህር ውስጥ ሲገባ የነቢዩ ቃል ይፈጸም ዘንድ ዮርዳኖስ ወደ ኋላ ሸሸች በመዝሙር 113:5 ‘ባህርኒ ርእየት ወጎየት ወዮርዳኖስኒ ገብአ ድኅሬሁ አድባር አንፈርአጹ ከመሐራጊት። ትርጉም ‘አንቺ ባሕር የሸሸሽ አንቺም ዮርዳኖስ ወደ ኋላሽ የተመለሽ ምን ሆነሻል:: እናንተም ተራሮች እንደኮርማዎች ኮረብቶችሽ እንደጊደር ለምን ዘለላችሁ’ የተባለው የነቢዩ ቃል ይፈጸም ዘንድ::

ጌታ ሲጠመቅ ተራሮች ሽቅብ ዘለሉ ውሆች ተናወጹ የመጣው ፈጣሪያቸው አምላካቸው ነውና:: በኋላ ግን በሰውነቱ ተናግሮ በአምላክነቱ አጽንቷቸው በእደ ዮሐንስ ተጠመቀ:: ተጠምቆ ከውሃ ሲወጣ በማቴ 3:13 -17 እንደተጻፈው አብ በደመና ሆኖ ‘ዝንቱ ውእቱ ወልድየ ዘአፈቅር ሎቱ ስምዕዎ’ የምወደው ልጄ ይህ ነው እርሱን ስሙት ብሎ የባህርይ ልጅነቱን መስክሮለታል:: መንፈስ ቅዱስም በአምሳለ ርግብ ፀዓዳ ሆኖ ወርዶ በራሱ ላይ አርፎበታል::

፩. ከፍ ብሎ በ 31 ዝቅ ብሎ በ 29 ዓመት አለመጠመቁ በ 30 ዓመቱ መጠመቁ አዳም የ 30 ዓመት ጎልማሳ ሆኖ በ 40 ቀን አግኝቶ ያጣትን ልጅነት ለማስመለስ ነው::

፪. አምላክ ሰው ሲሆን በሰው እጅ መጠመቁ ትህትናውን ለመግለጽ ነው::

፫. ዮሐንስን አስጠርቶ ካለበት ቦታ መጠመቅ ሲችል ዮሐንስ ወዳለበት ወደ ገሊላ ሄዶ መጠመቁ ሥርዓትን ለማስተማር ነው:: ምክንያቱም ዮሐንስን አስጠርቶ ተጠምቆ ቢሆን ኖሮ ዛሬ መኳንንቱ መሳፍንቱ ባለስልጣናቱ እቤታችን ድረስ መጣችሁ አጥምቁን ባሉ ነበር::

፬. በማር በወተት መጠመቅ ሲችል በውሃ የተጠመቀበት ምክንያት ማር ሲልሱት ወተትም ሲጠጡት እንጅ ሊታጠቡባቸው አልተፈጠሩምና:: አንድም በማር በወተት ተጠምቆ ቢሆን ኖሮ ማርና ወተትን ድሆች ስለማያገኟቸው ሳይጠመቁ ይቀሩ ነበርና:: ጥምቀት የተሰራ ለሁሉም ሰው ነውና ደሃውም ሀብታሙም በሚያገኘው በውሃ ተጠመቀ:: አንድም በውሃ የተጠመቀበት ምክንያት ውሃ ቢጠጡት ያረካል በታጠቡበት ያነጻል ጥምቀትም ከኃጢአታችን ያነጻናልና:: ጥምቀትም ከሥላሴ መወለዳችንን ቁልጭ አድርጎ ያሳያልና::

፭. ብዙ ባሕር እያለ የዮርዳኖስን ባሕር የመረጠው የዕዳ ደብዳቤያችንን ሊያጠፋልን ነው:: ምክንያቱም ዲያብሎስ አዳምና ሔዋንን የጨለማ መጋረጃ ጋርዶ ‘አዳም ገብሩ ለዲያብሎስ ሔዋን ዓመቱ ለዲያብሎስ’ ብላችሁ ጽፋችሁ ብትሰጡኝ አገዛዜን አቀልላችሁ ነበር ሲላቸው ይህንን ጽፈው ሰጡት:: ዲያብሎስ ያንን በሁለት ቀርጾ ጽፎ አንዱን በዮርዳኖስ አንዱን በሲኦል ጥሎት ነበርና በዮርዳኖስ የጣለውን እንደሰውነቱ ረግጦ እንደምላክነቱ አቅልጦ አጥፍቶልናል:: በሲኦል የጣለውን ጌታ በዕለተ ዐርብ በተሰቀለ ጊዜ በአካለ ነፍስ አጥፍቶልናል:: ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ <<በጥምቀትም ከእርሱ ጋር ተቀብራችሁ በጥምቀት ደግሞ ከሙታን ባስነሣው በእግዚአብሔር አሠራር በማመናችሁ ከእርሱ ጋር ተነሣችሁ። እናንተም በበደላችሁና ሥጋችሁን ባለመገረዝ ሙታን በሆናችሁ ጊዜ ከእርሱ ጋር ሕይወትን ሰጣችሁ። በደላችሁን ሁሉ ይቅር አላችሁ። በእኛ ላይ የነበረውን የሚቃወመንንም በትእዛዛት የተጻፈውን የዕዳ ጽሕፈት ደመሰሰው። እርሱንም በመስቀል ጠርቆ ከመንገድ አስወግዶታል።>> እንዳለን ቆላ ፪:፲፪-፲፬

ሌሊት በ 10 ሰዓት መጠመቁ ምስጢረ መንግስቱን ለመግለጽ ነው:: በቀን ተጠምቆ ቢሆን ኖሮ መንፈስ ቅዱስ በአምሳለ ርግብ ሲወርድ ሰዎች ይህ መናኛ ርግብ እንጅ መንፈስ ቅዱስ አይደለም ይሉ ነበር::

የተወደዳችሁ ሕዝበ ክርስቲያን:- በየዓመቱ የምናከብረው የጥምቀት በዓል ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ጥምቀት አንዲት ናት አንዳለው (ኤፌ ፬:፭) አባቶችም በሃይማኖት ጸሎት ላይ ወነአምን በአሀቲ ጥምቀት ለሥርየተ ኃጢአት ብለው እንዳስተማሩን ጥምቀት አንዲት የማትደገም የማትከለስ መሆኗን አምነን ከጥምቀት በዓሉም በረከት ለማግኘት ነው:: የአባቶቻችን አምላክ ልዑል እግዚአብሔር በዓሉን የሰላም የፍቅር ያድርግልን:: ከበዓለ ጥምቀቱም በረከት ረድኤት እንዲከፍለን የእናታችን የድንግል ማርያም አማላጅነት አይለየን።

የደብሩ አገልጋይ መምህር በቃሉ ዳዊት