ገብር ኄር
ገብር ኄር
በመጋቤ ሐዲስ ፍቅረ ማርያም ባዘዘው
በቦሌ መንበረ ብርሃን ቅዱስ እግዚአብሔር አብ ቤተክርስቲያን የሐዲስ ኪዳን የትርጓሜ መምህር
እንደሚታወቀው የዐቢይ ጾም ስድስተኛ ሳምንት ገብር ኄር በመባል ይታወቃል፡፡ ለመሆኑ ገብር ኄር ሲባል ምን ማለት ነው? ገብር ኄር ሲባል ታማኝ አገልጋይ ማለት ሲሆን ታመኝነቱም ለራሱና ለፈጣሪው ነው፡፡ ስለዚህ ለዛሬው ርእስ የምናደርገው ታማኝነት በሚል ነው፡፡
ታማኝነት 25፤21
ቅዱስ ቃሉ እንዲህ ይላል፡- ማቴ.25፤14-23 ወደ ሌላ አገር የሚሄድ ሰው ባሮቹን ጠርቶ ያለውን ገንዘብ እንደ ሰጣቸው እንዲሁ ይሆናልና፤ ለእያንዳንዱ እንደ ዓቅሙ፥ ለአንዱ አምስት መክሊት ለአንዱ ሁለት ለአንዱም አንድ ሰጠና ወደ ሌላ አገር ወዲያው ሄደ። አምስት መክሊትም የተቀበለው ሄዶ ነገደበት ሌላም አምስት አተረፈ፤ እንዲሁም ሁለት የተቀበለው ሌላ ሁለት አተረፈ። አንድ የተቀበለው ግን ሄዶ ምድርን ቈፈረና የጌታውን ገንዘብ ቀበረ። ከብዙ ዘመንም በኋላ የእነዚያ ባሮች ጌታ መጣና ተቆጣጠራቸው። አምስት መክሊት የተቀበለውም ቀረበና ሌላ አምስት መክሊት አስረክቦ። ጌታ ሆይ፥ አምስት መክሊት ሰጥተኸኝ ነበር፤ እነሆ፥ ሌላ አምስት መክሊት አተረፍሁበት አለ። ጌታውም። መልካም፥ አንተ በጎ ታማኝም ባሪያ፤ በጥቂቱ ታምነሃል፥ በብዙ እሾምሃለሁ፤ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ አለው። ሁለት መክሊትም የተቀበለው ደግሞ ቀርቦ። ጌታ ሆይ፥ ሁለት መክሊት ሰጥተኸኝ ነበር፤ እነሆ፥ ሌላ ሁለት መክሊት አተረፍሁበት አለ። ጌታውም። መልካም፥ አንተ በጎ፥ ታማኝም ባሪያ፤ በጥቂቱ ታምነሃል፥ በብዙ እሾምሃለሁ፥ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ አለው። በአንጻሩም ደግሞ የተቀበለውን ቀብሮ ያኖረ በመጨረሻም የተፈረደበት ሰው አለ፡፡
እኛ ማየት የሚገባን ሠርቶ ያተረፈውን ነው፡፡ ብዙ ጊዜ የሰው ልጆች ሰርተው ያተረፉትን ሳይሆን የተቀበሉትን ሳያተርፉ የቀሩትን ሰዎች አብነት ሲያደርጉ ይስተዋላሉ፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ ግን የሠሩትን ወይንም ያተረፉትን የምንመለከት ከሆነ ለተቀበልነው ዓላማ ብቁዎች እንሆን ነበር፡፡ እንግዲህ በዚህ ምዕራፍ ውስጥ የምንመለከተው አንድ ቁም ነገር አለ፡፡ እርሱም ታማኝ መሆንን ነው፡፡ ታማኝነት ለራስም ለወንድምም ለፈጣሪም እንዲሁም ለአገርም ይጠቅማል፡፡ ወንጌሉ እምደሚነግረን አንድ ባዕለ ጸጋ ለሦስት ሰዎች ለእያንዳንዳቸው እንደየአቅማቸው ለእንደኛው አምስት፤ ለሁለተኛው ሁለት፤ ለሦስተኛው አንድ መክሊት ወይንም ገንዘብ ሰጣቸው፡፡ የተቀበሉትም እንዲሠሩበት ነበር፡፡ ባለ አምስቱና ባለሁለቱ አትርፈው ሲመሰገኑ ባለ አንዱ ግን የተቀበለውን ነገር መሬት ውስጥ ቆፍሮ አስቀመጠው፡፡ እንደሚታወቀው እግዚአብሔር አባታችን ለእኛ ሁሉን ነገር አድርጓል ያጎደለብን ነገር የለም፡፡ ለአንዱ አንድ መክሊት መስጠቱ እርሱ ሁላችን አንድ የአዳም ዘሮች መሆናችንን ያጠይቃል ሁለት መስጠቱ ደግሞ በእኛ ውስጥ ፍቅረ ቢጽና ፍቅረ እግዚአብሔር መኖሩን ያጠይቃል አምስት መስጠቱ ደግሞ በእኛ ውስጥ ያሉ አምስት የስሜት ዕዋሳትን ያጠይቃሉ ማለት ነው፡፡
እንግዲህ ነገሩ እንዲህ ከሆነ ባለ ዕዳዎቹ እኛው ነን ማለት ነው ሁሉም ሰው ሁሉን ተቀብሏል ግን ሁሉም አትራፊ ሳይሆን አጉዳይ ሆኗል፡፡ ባለ አንዱን እንውሰድ የሰው ልጀች አንድ የአዳም ዘሮች መሆናችን በዚህ ወቅትና በዚህ ሰዓት የተረሳ ወይንም የተካደ በሚመስል ሁኔታ ሰው ሁሉ ከእግዚአብሔር አንድነት ፍቅር ወጥቷል አንዱ አንዱን ገፍቶ ሁሉም ነገር የእኔ የሚል አባዜ በውስጡ ነግሧል፡፡ ስለአንድነት ከመስበክ ይልቅ ስለመለያት የሚሰብከው በዝቷል፤ አንድነትን የሚሰብከው ኢትዮጵያዊነት ውስጣችን ጠፍቷል በአጠቃላይ በሚባል ሁኔታ የሰዎች እይታ ከፈጣሪ እይታ ውጭ ሆኗል ምክንያቱም ሁላችን አንድ አባት ካለን እኛ ሁላችንም አንድ ነን እንጅ ሁለት አይደለንም ምን አልባትም ሁለት ነን ብለው የሚያስቡት ከአንድ አባት ውጭ የተወለዱ ሲሆኑ ብቻ ነው፡፡
የእግዚአብሔር ልጆች በአንድ መንፈስ፤ በአንድ ኃይል፤ በአንድ ዕውነት ሥር ያደጉ ናቸውና ሕይወታቸውም እንዲሁ ነው፡፡ በዚህ ዓለም ውስጥ ሲኖሩ ራሳቸውን በእግዚአብሔር የህግ ጥላ ሥር የሚያስጠልሉ፤ ዋሽተው ቀምተው ከመኖር ይልቅ በአንድ በዕውነት መንገድ ውስጥ ኖረው ለመንግሥቱ የተዘጋጁ፤ በንግግር ሱስ የተጠመዱ ሳይሆኑ ዕውነቱን ዕውነት ሐሰቱን ሐሰት በሚለው ዕውነተኛ ወንጌል ውስጥ በቅለው ያደጉ፤ ከመለያየት መንፈስ ይልቅ የአንድነትና የፍቅር መንፈስ ውስጣቸውን ያበለጸጋቸው፤ ከዚህ ዓለም ውጭ ዕውነተኛው ዓለም እንዳለ የተገነዘቡ፡፡ ከጊዜያዊ ጥቅም ይልቅ ዘለዓለማዊውን የእግዚአብሔርን መንግሥት የሚያስቡ፤ የአንድ አባት ያውም የእግዚአብሔር ልጆች እንደመሆናቸው መጠን በእርሱ ፍቅር ውስጥ የሚኖሩ እኒህ ናቸው የእንድነትን መክሊት ከፈጣሪያቸው አስቀድሞ በተፈጥሮ ከዚያም በሞቱ ተቀብለው በምድራዊ ሀሳብ ማንነት ሰማያዊውን መክሊት ሳይቀብሩ ሰማያዊ ሀብት እንደመሆኑ መጠን በአንድ ፍቅር ጠብቀው ያስጠበቁ ዕውነተኞች ክርስቲያኖች እነኝህ ናቸው፡፡ በአንጻሩም የአንድነት ፍቅር ያልገባቸው በተፈጥሮና እና እንዲሁ የሞት ዋጋ የተከፈለበትን ማንነት ተቀብለውት ነገር ግን ለተቀበሉት ነገር ብቁ ሳይሆኑ ቀብረው ያስቀሩ የፈጣሪያቸውን ማንነት የዘነጉ ናቸውና ጥያቄው አይቀርም በተፈጥሮና በሞት ውስጥ አልፌ የሰጠውህን ማንነቴን አምጣ ወይንም የት ጣልከው ሲባል መልስ ማጣት ይከብዳል፡፡ ሌላ ነገር ሳይሆን የተቀበሉትን ነገር ለተቀበሉለት ዓላማ ብቁ ማድረግ አለመቻል ያስጠይቃልና ነው፡፡
በዚህ የበሽታ አባዜ ሁሉም ታላቁም ታናሹም ቁስለኛ ሆኗል፡፡ ኢሳ.1፤6 ከእግር ጫማ አንስቶ እስከ ራስ ድረስ ጤና የለውም ቍስልና እበጥ የሚመግልም ነው አልፈረጠም፥ አልተጠገነም፥ በዘይትም አልለዘበም። ይህ ማለት መሪውም ተመሪውም የፍቅር ዘይት ጎሎታል በነገር እበጥ ተመትቷል ራሱን ለመጠገን በአንድ የፍቅር ሰንሰለት ውስጥ መግባት አለበት፡፡ እንዲህ ሲሆን ወይንም ለተቀበለነው ዓላማ ታማኝ ሆነናልና ዋጋው ይጠብቀናል፡፡ ብዙ ጊዜ ሰዎች ባለ አንድ ሲባል ትንሽ ነገር አድርገው ይቆጥሩታል ነገር ግን እንደዛ አይደለም እግዚአብሔር ትንሽ ሀብት የለውም፡፡ ትልቁ ሰው ይህን ነገር ሁሉ አድርግ ተብሎ የታዘዘው የፈጣሪ የእጅ ሥራ ነው፡፡ ይህ ትልቅ ሰው መሥራት የሚገባውም ትልቅ ሥራ ነውና ከፍቅርና ከአንድነት የበለጠ ትልቅ ሥራም የለምና፡፡
ከላይ እንዳልነውም ባለሁለቱም እግዚአብሔርን መውደድና ባልንጀራን መውደድ ናቸው፡፡ ሉቃስ.10፤30 እንዲህ ይላል፡- አንድ ሰው ከኢየሩሳሌም ወደ ኢያሪኮ ወረደ በወንበዴዎችም እጅ ወደቀ፤ እነርሱም ደግሞ ገፈፉት ደበደቡትም በሕይወትና በሞት መካከልም ትተውት ሄዱ። ድንገትም አንድ ካህን በዚያ መንገድ ወረደ አይቶትም ገለል ብሎ አለፈ። እንዲሁም ደግሞ አንድ ሌዋዊ ወደዚያ ስፍራ መጣና አይቶት ገለል ብሎ አለፈ። አንድ ሳምራዊ ግን ሲሄድ ወደ እርሱ መጣ አይቶትም አዘነለት፥ ቀርቦም ዘይትና የወይን ጠጅ በቍስሎቹ ላይ አፍስሶ አሰራቸው፥ በራሱ አህያም ላይ አስቀምጦት ወደ እንግዶች ማደርያ ወሰደው ጠበቀውም። በማግሥቱም ሁለት ዲናር አውጥቶ ለባለቤቱ ሰጠና። ጠብቀው፥ ከዚህም በላይ የምትከስረውን ሁሉ እኔ ስመለስ እከፍልሃለሁ አለው። ይህ ነው ፍቅረ ቢጽና ፍቅረ እግዚአብሔር ማለት ሁለት ዲናር ሰጠው ሲል ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው ሆኖ በሞቱ እኛን አድኖ በመጨረሻም የሰጠን ነገር ቢኖር እነኝህ ሁለቱን ነገር ነው፡፡ ትርፋማ ከሆን የምናገኘው ዋጋ ይጠብቀናል ማለት ነው፡፡
ባለ አምስት ሲባል በተፈጥሮ የተቀበልናቸው የስሜት ሕዋሳት የምንላቸው ናቸው፡፡ የተቀበልናቸው በጎ ሥራ ልንሠራባቸው ነው፡፡ አዳም በእነዚህ የስሜት ሕዋሳት በደለ ክርስቶስ በመቸንከርና በሞቱ ካሳ ከፈለለት፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ በቅዳሴው ተናግሮታል አዳምን የፈጠሩ እጆች በመስቀል ላይ ተቸነከሩ በማለት ለሕዋሳቱ በአጠቃላይ የከፈለለትን ዋጋ ይዘረዝራል፡፡ ይህ ማንነት የእኛ ሳይሆን የፈጣሪ ነው፡፡ እኛ አደራ እንደመቀበላችን የተቀበልነውን አደራ በንጽሕና መጠበቅ ነው፡፡ ሕዋሳቶቻችን በምግባር፤ በትሩፋት፤ በጾም ትርፋማ ከሆኑ በዝች በንትሿ በምትጠፋው ዓለም ሳይሆን ለነገው ሰማያዊ ሕይወት ራስን ማዘጋጀት ይሆናል፡፡ በአጭር ለማድረግ እንዳንዱ ሰው እነኝህ ሀብቶች በውስጡ አሉ እስከሠራባቸው ድረስ የማያልፍና የማያልቅ ዋጋ ያገኝባቸዋል በአንጻሩም ካልሠራባቸው ጥያቄ አይቀሬ ነው፡፡ በተቀበልነው ነገር ታማኝ እንድንሆን አምላከ ቅዱሳን ይርዳን፡፡
ይቆየን
