ቅድስት

                                              ቅድስት

በመጋቤ ሐዲስ ፍቅረ ማርያም ባዘዘው

በቦሌ መንበረ ብርሃን ቅዱስ እግዚአብሔር አብ ቤተክርስቲያን የሐዲስ ኪዳን የትርጓሜ መምህር

 

የዐቢይ ጾም ሁለተኛው ሳምንት ቅድስት ይባላል፡፡ ይህም ሲባል በአጠቃላይ ሁሉም ሳምንታት ከተሰየመላቸው አንዱ ነው ማለት ነው፡፡ ይህም ቅድሰት ሲባል የተለየ ወይንም የከበረ የሚለውን ትርጉም የሚሰጥ ሲሆን ይህ ማለት ግን ሌሎች ቀኖች የተለዩ ወይንም የከበሩ አይደሉም ማለት አይደለም ፡፡ የዕለቱ ስያሜ ነው እንጂ፡፡ በዚህ ቀን የሚነበበው ወንጌል እንዲሁም የዕለቱ ምስባክ ዕለቱን በተመለከተ የሚነበቡ ወይንም የሚነገሩ ናቸው፡፡ ለዛሬው  ርእስ የምናደርገው በማቴዎስ ወንጌል ያለውን ነው ይህም በዕለቱ የሚነበበው ወንጌል ነው፡፡

‹‹ወሶበ ትጸውሙ ኢትኩኑ ከመ መደልዋን›› በምትጾሙበት ጊዜ እንደ ግብዞች አትሁኑ ማቴ.6፤16

ጾም ማለት ማቆም ወይንም መከልከል ማለት ነው፡፡ ሰው ጾምን ሲጾም የሚከለከልባቸው ነገሮች አሉ፡፡ ፍትሐ ነገሥት አንቀጽ 15 አንድ ሰው ሰው ጾመ ሲባል ከምን ከምን መከልከል አለበት ሲባል፡፡

ከምግብ ይህንም ፍትሐ ነገሥት አንቀጽ 15 ጾም ማለት በታወቀ ጊዜና በታወቀ ሰዓት ከመብልና ከመጠጥ የምንከለከለው መከልከል ነው ሲል ይገልጸዋል፡፡ በታወቀ ጊዜ ሲባል ሰባቱን አጽዋማት ማለት ሲሆን በታወቀ ሰዓት ሲባል ጾመን የምንቆይበትን ሰዓት ሲገልጽልን ነው፡፡ ይህንም ዘጠኝ ሰዓት ይላል ምክንያቱም አንድ የኦርቶዶክስ አማኝ ውሎ አስቀድሶ ሥጋወደሙን መቀበል ስላለበት ነው ፡፡ የአንድ አማኝ የኦርቶዶክስ ልጅ ሕይወቱ ከሥጋ ወደሙ የተለየ አይደለም፡፡ ከሥጋ ወደሙ የተለየ ሰው ተሸናፊ ነው፤፤ ያገኘው ጠላት ሁሉ (የአጋንንት ሠራዊት) ያሸንፈዋል በፍትወተ ሥጋ ሀሳብ ይሸነፋል፡፡ በሥጋ ወደሙ የታተመ ማንነት ያለው ሰው ግን ድል ይነሳል እንጅ ድል አይነሳም፡፡ ራዕይ 7፤9-17 እንዲህ ይላል፡፡ ከዚህ በኋላ አየሁ፥ እነሆም፥ አንድ እንኳ ሊቆጥራቸው የማይችል ከሕዝብና ከነገድ ከወገንም ከቋንቋም ሁሉ እጅግ ብዙ ሰዎች ነበሩ፤ ነጭ ልብስም ለብሰው የዘንባባንም ዝንጣፊዎች በእጆቻቸው ይዘው በዙፋኑና በበጉ ፊት ቆሙ፤ በታላቅም ድምፅ እየጮሁ። በዙፋኑ ላይ ለተቀመጠው ለአምላካችንና ለበጉ ማዳን ነው አሉ። መላእክቱም ሁሉ በዙፋኑና በሽማግሌዎቹ በአራቱም እንስሶቹ ዙሪያ ቆመው ነበር፤ በዙፋኑም ፊት በግምባራቸው ተደፉ፥ ለእግዚአብሔርም እየሰገዱ። አሜን፥ በረከትና ክብር ጥበብም ምስጋናም ውዳሴም ኃይልም ብርታትም ከዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ ለአምላካችን ይሁን፤ አሜን አሉ። ከሽማግሌዎቹም አንዱ ተመልሶ፦ እነዚህ ነጩን ልብስ የለበሱ እነማን ናቸው? ከወዴትስ መጡ? አለኝ። እኔም። ጌታ ሆይ፥ አንተ ታውቃለህ አልሁት። አለኝም። እነዚህ ከታላቁ መከራ የመጡ ናቸው፥ ልብሳቸውንም አጥበው በበጉ ደም አነጹ። ስለዚህ በእግዚአብሔር ዙፋን ፊት አሉ፥ ሌሊትና ቀንም በመቅደሱ ያመልኩታል፥ በዙፋኑም ላይ የተቀመጠው በእነርሱ ላይ ያድርባቸዋል። ከእንግዲህ ወዲህ አይራቡም፥ ከእንግዲህም ወዲህ አይጠሙም፥ ፀሐይም ትኵሳትም ሁሉ ከቶ አይወርድባቸውም በዙፋኑ መካከል ያለው በጉ እረኛቸው ይሆናልና፥ ወደ ሕይወትም ውኃ ምንጭ ይመራቸዋልና፤ እግዚአብሔርም እንባዎችን ሁሉ ከዓይናቸው ያብሳል። ይህ ነው የማይጠፋ ማንነት በሥጋ ወደሙ የታተመ በጾም የተወሰነ፡፡ ሰው ሲጾም ሲፀልይ ሕይወቱ ከሥጋ ወደሙ ጋር የታተመ ነው፡፡

2 ቅዱስ ያሬድ ይጹም ዓይን፤ ይጹም ልሳን፤ ይጹም አፍ፤ ዕዝንኒ ይጹም እምሰሚዓ እሱም፡፡ ዓይን ይጹም አንደበት ይጹም አፍ ይጹም ጀሮም መጥፎ ነገር ከመስማት ይከልከል ይላል፡፡ በአጠቃላይ ጾም ሲባል መላ ሰውነታችን ነው የሚጾመው ማለት ነው፡፡ ቅድስት የተባለም ለዚህ ነው፡፡ የተለየ ጾም፤የተለየ ማንነት፤ የተለየ ስብእና ሊኖረን የሚችለው እንዲህ ያለ እውነተኛ ጾም ስንጾም ነው፡፡ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ክብር ይግባውና በማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 5፤6 ላይ እንዲህ ሲል አስተምሮ ነበር፡፡ ዛሬ ስለጽድቅ የሚራቡ ብጹዓን ናቸው ይጠግባሉና፡፡ እንግዲህ ዛሬ ስንል የዕኛ ዘመን ነው፡፡ ዛሬ ዕድሜ ነው፤ ዛሬ የተባለ ወጣቱም የእርሱ ዕድሜ አሁን ያለበት ዛሬ ይባላል፡፡ ሁሉም ሰው አሁን ያለበት ዕድሜ ለእርሱ ዛሬ ነው፡፡ ዛሬ በዕድሜው ሥራን የሚሠራ የሚጾም የሚፀልይ ዋጋ አለው፡፡ የሚገርመው ነገር ደግሞ እርሱ ባለቤቱ ዛሬ የሚራቡ እያለ እየተናገረ ለነገ የምናስብ ብዙ በመሆናችን ነው፡፡ ዛሬ መሥራት ስንችል፤ ዛሬ መስገድ ስንችል በአጠቃላይ ማኛውንም መንሰሳዊ ነገር ዛሬ ማድረግ ስንችል ሁሉንም ነገር ለነገ እንላለን እኛ የምናውቀው ዛሬን እንጅ ነገን አይደለም፡፡ ነገ ሌላ ነውና፡፡ ሁሉም ሰው መንፈሳዊን ተግባር ዛሬ መፈጸም አለበት ነገ በመጨረሻው ሰዓት ዋጋው ይጠብቀው ዘንድ፡፡ ሰው ሁለንተናው ሲጾም ለደከመበት ዋጋው ይሰጠዋል ብዙ ጊዜ እየጾሙ ነገረኛ የሆኑ ወንድሞቻቸውን የሚያስቀይሙ በሐሜት የሚኖሩ ብዙ ሰዎች አሉ አንደበታቸው ሁሉ ሲጾም ነው ዋጋ የሚያገኙት፡፡

  1. እውነተኛ ፍርድን በመስጠት፡- ኢሳይያስ 58፤1 በኃይልህ ጩኽ፥ አትቈጥብ፥ ድምፅህን እንደ መለከት አንሣ፥ ለሕዝቤ መተላለፋቸውን ለያዕቆብ ቤትም ኃጢአታቸውን ንገር። ነገር ግን ዕለት ዕለት ይሹኛል መንገዴንም ያውቁ ዘንድ ይወድዳሉ ጽድቅን እንዳደረጉ የአምላካቸውንም ፍርድ እንዳልተዉ ሕዝብ እውነተኛውን ፍርድ ይለምኑኛል፥ ወደ እግዚአብሔርም ለመቅረብ ይወድዳሉ። ስለ ምን ጾምን፥ አንተም አልተመለከትኸንም? ሰውነታችንንስ ስለ ምን አዋረድን፥ አንተም አላወቅህም? ይላሉ። እነሆ፥ በጾማችሁ ቀን ፈቃዳችሁን ታደርጋላችሁ፥ ሠራተኞቻችሁንም ሁሉ ታስጨንቃላችሁ። እነሆ፥ ለጥልና ለክርክር ትጾማላችሁ በግፍ ጡጫም ትማታላችሁ ድምፃችሁንም ወደ ላይ ታሰሙ ዘንድ ዛሬ እንደምትጾሙት አትጾሙም። እኔ የመረጥሁት ጾም ይህ ነውን? ሰውስ ነፍሱን የሚያዋርደው እንደዚህ ባለ ቀን ነውን? በውኑ ራሱን እንደ እንግጫ ዝቅ ያደርግ ዘንድ ማቅንና አመድንም በበታቹ ያነጥፍ ዘንድ ነውን? በውኑ ይህን ጾም፥ በእግዚአብሔርም ዘንድ የተወደደ ቀን ትለዋለህን? እኔስ የመረጥሁት ጾም ይህ አይደለምን? የበደልን እስራት ትፈቱ ዘንድ፥ የቀንበርንስ ጠፍር ትለቅቁ ዘንድ፥ የተገፉትንስ አርነት ትሰድዱ ዘንድ፥ ቀንበሩንስ ሁሉ ትሰብሩ ዘንድ አይደለምን? እንጀራህንስ ለተራበ ትቈርስ ዘንድ፥ ስደተኞቹን ድሆች ወደ ቤትህ ታገባ ዘንድ፥ የተራቈተውንስ ብታይ ታለብሰው ዘንድ፥ ከሥጋ ዘመድህ እንዳትሸሽግ አይደለምን? የዚያን ጊዜ ብርሃንህ እንደ ንጋት ይበራል፥ ፈውስህም ፈጥኖ ይበቅላል፥ ጽድቅህም በፊትህ ይሄዳል፥ የእግዚአብሔርም ክብር በኋላህ ሆኖ ይጠብቅሃል። የዚያን ጊዜ ትጠራለህ እግዚአብሔርም ይሰማሃል ትጮኻለህ እርሱም፦ እነሆኝ ይላል። ከመካከልህ ቀንበርን ብታርቅ፥ ጣትህንም መጥቀስ ብትተው፥ ባታንጐራጕርም፥ ነፍስህንም ለተራበ ብታፈስስ፥ የተጨነቀውንም ነፍስ ብታጠግብ፥ ብርሃንህ በጨለማ ይወጣል ጨለማህም እንደ ቀትር ይሆናል። እግዚአብሔርም ሁልጊዜ ይመራሃል ነፍስህንም በመልካም ነገር ያጠግባል አጥንትህንም ያጠናል አንተም እንደሚጠጣ ገነት፥ ውኃውም እንደማያቋርጥ ምንጭ ትሆናለህ። ከዱሮ ዘመን የፈረሱት ስፍራዎች ይሠራሉ፥ የብዙ ትውልድም መሠረት ይታነጻል አንተም። ሰባራውን ጠጋኝ፥ የመኖሪያ መንገድን አዳሽ ትባላለህ። ፈቃድህን በተቀደሰው ቀኔ ከማድረግ እግርህን ከሰንበት ብትመልስ፥ ሰንበትንም ደስታ፥ እግዚአብሔርም የቀደሰውን ክቡር ብትለው፥ የገዛ መንገድህንም ከማድረግ ፈቃድህንም ከማግኘት ከንቱ ነገርንም ከመናገር ተከልክለህ ብታከብረው፥ በዚያን ጊዜ በእግዚአብሔር ደስ ይልሃል፥ በምድርም ከፍታዎች ላይ አወጣሃለሁ፥ የአባትህንም የያዕቆብን ርስት አበላሃለሁ የእግዚአብሔር አፍ ተናግሮአልና።

ትክክለኛ ጾም ከሆነ ዋጋ አለው ያለበለዚያ ድግሞ ያስወቅሳል ማለት ነው ሰውን እያስለቀሱ የሚጾሙት ጾም ከባድ ሰለሆነ ሁላችንም በፍቅር መጾም እንዳለብን ነው የሚነገረን፡፡ ለዚህ ጾም ክርስቶስን ወልዳ ምክንያት የሆነችን ወላዲተ አምላክ በምላጃዋ አትለየን አሜን፡፡

 

ይቆየን፡፡