ስደት
ከተወለድኩበት ከቀየ ከመንደሬ፤
ድኼ ካደግኩበት ከትውልድ ሠፈሬ፤
ሀ ሁ ን ከጻፍኩበት ፊደልን ቆጥሬ፤
ችግር ቢያሰቅቀኝ አውጭኝ አልኩኝ እግሬ፡፡
ቆይቼ እስክደርስ ከማላውቀው ሀገር፤
በመንገድ የሆንኩት የማልረሳው ነበር፡፡
በባዕድ ሀገር ላይ ተባልኩኝ እንግዳ፤
እስክለምደው ድረስ በጥቂት ልረዳ፡፡
ነፍሴ ተረጋግታ ማስተዋል ሲመጣ፤
የተቀበረብኝ የማንነቴ ፍም ሊያቃጥለኝ ወጣ፡፡
ጥያቄን ጠየኩኝ ማድመጥ ለወደደ፤
እስከዛሬ ድረስ ማን ከየት ወደየት እንደተሰደደ፡፡
የስደትን ምስጢር የስደትን ነገር፤
በዝርዝር አብራርቶ የሚችል መናገር፤
ለካስ በእጄ ያለው መጽሐፍ ቅዱስ ነበር፡፡
የመጀመሪያው ሰው በለስን ባደማ፤
ወጥቶ ተሰደደ ከሕይወት ከተማ፡፡
የጥፋትም ውሃ በምድር ላይ መልቶ፤
ኖኅን አሰደደው መርከብ አስገብቶ፡፡
አብርሃምን ጠራው ፈጣሪው እግዚአብሔር፤
ካራንን እንዲለቅ የጣዖቷን ሀገር፡፡
ይስሃቅና ያዕቆብም እንደዚሁም ዮሴፍ ስደትን ቀመሱ፤
እርሱ ፈቅዷልና በተሰደዱበት ስሙን አወደሱ፡፡
አይ ስደት…! ህዝበ እስራኤልን ከከነዓን አስወጣ፤
በግብፅ ባርነት ተገዝቶ መኖርን መከራን አመጣ፡፡
ረሀብን ሸሽተው በግብፅ ቢሰደዱ፤
በባርነት ቀንበር አጅጉን ተጎዱ፡፡
አይ ስደት…! ውለታዉን ረስተው በደልን ቢያበዙ፤
ህዝበ እስራኤል በባቢሎን ምርኮ በግዞት ተያዙ፡፡
ያለ ውዴታቸው በግድ ተሰደዱ፤
በባዕድ ሀገርም ሊያመልኩት ወደዱ፡፡
ይህን ሁሉ ስደት በውስጤ ሳብላላ፤
ለካስ ሌላም አለ ከሁሉም የጎላ፡፡
የወደቀ አዳምን ሊያድን በወደደ፤
ኢየሱስ ክርስቶስ በግብፅ ተሰደደ፡፡
አዝላው ተሰደደች አዛኝት እናቱ፤
ዮሴፍም ሰሎሜም አብረው ተንገላቱ፡፡
ሐዋርያት አበውም ወንጌልን ሲሰብኩ፤
ለስደት መከራ ለእስር ተዳረጉ፡፡
ቢያሳድዷቸውም እልፍ እየገረፉ፤
በተሰደዱበት ወንጌልን አስፋፉ፡፡
የአላውያን መከራ ግፍ አሰቅቋቸው፤
ብዙዎች ተሰደዱ ከውድ ሀገራቸው፡፡
ነገር ግን… እምነት ተስፋ ፍቅር ውስጣቸው ስላሉ፤
በየደረሱበት መሠረትን ጣሉ፡፡
ወደ ቀድሞው ነገር ቶሎ ተመልሼ፤
በጥልቀት ባስበው መልሼ መልሼ፤
ለካስ…በእምነት መሰደድ ሁሌም የሚኖር ነው፤
የሥጋ ስደትም ነገም ዘላቂ ነው፡፡ –
ከእምነት መሰደድ ግን እጅግ የከፋ ነው፤
ከሲኦል የሚከት የዘለአለም ሞት ነው፡፡
በነፍስም መሰደድ እጅግ አሳዛኝ ነው፤
ሕይወትንም ጠልቶ ሲኦልን መምረጥ ነው፡፡
ይህን አሰብኩና አይኖቼን አቅንቼ፤
ጌታን ተማጸንኩት እጆቼን አንስቼ፡፡
ጌታ ሆይ… በሥጋ ብሰደድ ብርታትን አድለኝ፤
እንደ አባቶቼ በተሰደድኩበት ስምክን እንዳከብር የበቃሁ አድርገኝ፤
የነፍስን ስደት ግን ከቶ አታሳየኝ!
አባ ጥያቄ አለኝ
የደብረ ዘይት ቀን የዕለቱ ምስባክ፤
ከመቅደሱ ኆኅት በዜማ ሲሰበክ፤
በዝምታ ሆኜ ዲያቆኑን ባደምጠው፤
መልዕከቱን በልቤ እንደዚህ አስቀመጠው፡፡
“እግዚአብሔር በግልጥ ዳግም ይመጣል፤
ጌታ አምላካችንም ከቶ ዝም አይል
እሳትም በፊቱ ሲነድ ይታያል፡፡” ሲል
ቃሉ ከነዜማው ውስጤ ስለቀረ፤
ምላሽን የሚሹ ጥቂት ጥያቄዎች በልቤ አጫረ፡፡
በቅዳሴው ሥርዓት በትጋት ተጉዤ፤
ከፍጻሜው ደረስኩ ጥያቄዬን ይዤ፡፡
አባ…ጥያቄ አለኝ! አልኳቸው አሳልመው ሲሄዱ፤
ከወንበር ላይ አርፈው ሊሰሙኝ ወደዱ፡፡
ልጄ…በል እስኪ ንገረኝ ያለህን ጥያቄ፤
ከዚህ አለሁልህ ላደምጥህ ናፍቄ፡፡ … ሲሉኝ
አዳምን ሊያድነው አስቀድሞ የመጣ፤
ኧረ ለምንድን ነው ዳግመኛ የሚመጣ?
መላእክትን ትቶ ሰውን የፈለገው፤
ዳግመኛ ሊመጣ ለምን አስፈለገው? …ስላቸው
ይኸውልህ ልጄ፡-
ከእንግዲህ አይመጣም ዳግመኛ ሊወለድ፤
ሊያሳልፍ ነው እንጂ በሁሉ ላይ ሊፈርድ፡፡ …..ቢሉኝ እኔም
ለመፍረድ ከሆነ ይመጣል የሚሉት፤
እንሄድለት የለ ሁላችን ስንሞት! ……….ስላቸው
በወንጌል በመልእክት በራሱም አንደበት፤
ጻድቁን ሊያጸድቅ በኃጥኡ ለፈርድበት፤
መምጣቱ አይቀርም ተነግሯል በትንቢት፡፡… አሉኝ፡፡
ታዲያ አባ…
የምጽአቱ ነገር የሚከናወነው፤
የፈጣሪስ ፍርዱ መች ነው የሚሆነው?
ብዬ ጠየኳቸው ለማወቅ ጓጉቼ፤
ውስጤ የነበረውን ፍላጎት አውጥቼ፡፡
እርሳቸውም፡-
የአምላክን ጊዜና የምጽአትን ሰዓት፤
ከራሱ በስተቀር ከቶ ማንም አያውቃት፡፡
ትመጣለችና ቀኒቱ እንደ ሌባ፤
ተዘጋጅተን እንቆይ ንስሐም እንግባ፡፡
ለቅድመ ምጽአቱ የተተነበዩት ምልክት በሙሉ፤
ሁሉም ተፈጸሙ አንድ ባንድ እያሉ፡፡
በድንገት በቅጽበት በግልጽ በግርማ በኃይል ሲመጣ፤
የዘለአለም ሕይወት ጽድቅን እንዳናጣ፤
በቃሉም እንድንኖር መልካም እንድንሠራ፤
ዛሬም ለሁላችን አለብን አደራ፡፡……. ብለው ቢያብራሩልኝ
ውስጤ የነበሩ ውስጤ የተቀኙ፤
ብዙ ጥያቄዎች ምላሽን አገኙ፡፡
ከዓለም አውጥቶ ወደ ቤቱ ያመጣን፤
እንደዚህ የሚመክር አባት አያሳጣን፡፡ ….ብዬ ሳመሰግን
ጥያቄ ያላችሁ ወደዚህ አቅርቡ፤
ከእነጥያቄያችሁ እናንተም ቅረቡ፡፡
በፍቅር በትህትናም በቤቱ እንድትኖሩ፤
ሁሌም ከአባቶች ዘንድ መጥታችሁ ተማሩ፡፡
ለሁሉም ጥያቄ በቂ ምላሽ ያላት፡፤
ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ስንዱ እመቤት ናት!….አሉና
በል እግዚአብሔር ያበርታህ ልጄ ብለው አሰናበቱኝ

