መጻጉእ

መጻጉእ

በመጋቤ ሐዲስ ፍቅረ ማርያም ባዘዘው

በቦሌ መንበረ ብርሃን ቅዱስ እግዚአብሔር አብ ቤተክርስቲያን የሐዲስ ኪዳን የትርጓሜ መምህር

 

‹‹አልብየ ሰብእ›› ሰው የለኝም ዮሐንስ ወንጌል 5፤7

እንደሚታወቀው የዐቢይ ጾም አራተኛ ሳምንት መጻጉእ በመባል ይጠራል፡፡ ይህም ማለት በዕለቱ 38(ሠላሳ ስምንት) ዓመት በደዌ ምክንያት በአልጋ ላይ ተጣብቆ ይኖር የነበረ ሰው የተፈወሰበት ዕለት በመሆኑ መጻጉእ በመባል ይታወቃል፡፡

የዛሬው የዕለቱ ትምህርታችን ሰው የለኝም በሚል ይሆናል፡፡ ወንጌሉ እንዲህ ሲል ይገልጸዋል፡- በኢየሩሳሌምም በበጎች በር አጠገብ በዕብራይስጥ ቤተ ሳይዳ የምትባል አንዲት መጠመቂያ ነበረች፤ አምስትም መመላለሻ ነበረባት። በእነዚህ ውስጥ የውኃውን መንቀሳቀስ እየጠበቁ በሽተኞችና ዕውሮች አንካሶችም ሰውነታቸውም የሰለለ ብዙ ሕዝብ ይተኙ ነበር። አንዳንድ ጊዜ የጌታ መልአክ ወደ መጠመቂያይቱ ወርዶ ውኃውን ያናውጥ ነበርና፤ እንግዲህ ከውኃው መናወጥ በኋላ በመጀመሪያ የገባ ከማናቸው ካለበት ደዌ ጤናማ ይሆን ነበር። በዚያም ከሠላሳ ስምንት ዓመት ጀምሮ የታመመ አንድ ሰው ነበረ፤ ኢየሱስ ይህን ሰው ተኝቶ ባየ ጊዜ፥ እስከ አሁን ብዙ ዘመን እንዲሁ እንደ ነበረ አውቆ ልትድን ትወዳለህን? አለው። ድውዩም። ጌታ ሆይ፥ ውኃው በተናወጠ ጊዜ በመጠመቂያይቱ ውስጥ የሚያኖረኝ ሰው የለኝም ነገር ግን እኔ ስመጣ ሳለሁ ሌላው ቀድሞኝ ይወርዳል ብሎ መለሰለት። ኢየሱስ፦ ተነሣና አልጋህን ተሸክመህ ሂድ አለው፡፡ ወዲያውም ሰውዬው ዳነ አልጋውንም ተሸክሞ ሄደ፡፡በዚህ ምዕራፍ ውስጥ ትልቅ የምንማረው ነገር አለ ያም 38 ዓመት በአልጋ ተጣብቆ የሚኖር ሰው እግዚአብሔር ከእርሱ ጋራ ሲሆን መፈወሱን ነው፡፡ ሰዎች ለምን ሰው የለንም እንዲሉ ያደርጋቸዋል?

  1. ከደረሰባቸው ወይንም ከአጋጠማቸው ችግር አኳያ፡- ብዙ ጊዜ ሰው ከባድና ውስብስብ ነገር ሲገጥመው በአንጻሩም አለኝ የሚለው ሰው ከጎኑ ሲርቅ ከተስፋ መቁረጥ የተነሣ ሰው የለኝም ይላል፡፡ መጻጉእም 38 ዓመት ከአልጋ የተኛው ከሚጠመቅበት ቦታ የሚያደርሰው ሰው ባለማግኘቱ ተስፋ በወቁረጥ ሰው የለኝም ሲል ተደምጧል፡፡ እንደሚታወቀው የእግዚአብሔር መልአክ ውኃውን ወይንም መጠመቂያውን ከእግዚአብሔር ታዝዞ ያናውጠው (ይቀድሰው)  ነበር ያኔ አስቀድሞ የሚገባ ከደዌው ወይንም ከበሽታው ይፈወስ ነበር፡፡ በአንጻሩም ደግሞ ሰው የሌለው ከዛው ተኝቶ ይኖራል እንጅ የመፈወስ ዕድሉ አነሳ ነበር፡፡ መጻጉእ እንዲህ ባለ ሕይወት ውስጥ ሆኖ ነገር ግን ወደ መጠመቂያው የሚወስደው ሰው ያጣ ምስኪን ሰው ነበር፡፡ መጻጉእ ስሜትን የሚነካ ነገር የተናገረው ከነበረው የውስጥ ጉዳት የተነሣ ነበር፡፡ ለመሆኑ ስንት አይነት ደዌ ወይንም በሽታ አለ? እንደ አባቶቻችን አስተምህሮ ወደ አራት አይነት ደዌ አሉ ከእነዚህም መካከል ደዌ ዘኃጢአት፤ደዌ ዘመቅሰፍት፤ ደዌ ዘንጽሕ፤ ደዌ ዘዕሴት ናቸው፡፡ ደዌ ዘንጽሕ እንደ ጢሞቴዎስ ከማስተማር የተነሣ ሰውነታቸው ደርቆ የነበር ስለንጽሕናቸው የተቀበሉት ደዌ ነው ያም ማለት ለክብር የሚያበቃ ነው፡፡ ደዌ ዘዕሴትም እንደ ኢዮብ ነው እርሱም ዋጋ ያገኘበት በሽታ ወይንም ደዌ ነበር፡፡ ደዌ ዘመቅሰፍት እንደ ሄሮድስ በጥፋቱ በመቅሰፍት የሞተበት ነው፡፡ ደዌ ዘኃጢአት ደግሞ መጻጉእ እንደታመመበት ያለ ደዌ ወይንም በሽታ ነበር፡፡ መጻጉእ ሲጀመር ደዌው ከእግዚአብሔር ህግ በመውጣቱ ወይንም የእግዚአብሔርን ትዕዛዝ በመተላለፉ የመጣበት ደዌ ነበር፡፡ እንደሚታወቀው በብሉይ ኪዳን ሰው ኃጢአት ሲሠራ በሰውነቱ ደዌው ወይንም በሽታው ይታይ ነበር፡፡ በሐዲስ ኪዳን ግን ሰው ኃጢአት ሲሠራ በንስሐ የሚመለስ ሆኗል፡፡ እንግዲህ መጻጉእ 38 ዓመት በሙሉ ብቻውን ሆኖ የሰው ያለህ ሲል የቆየው ምን አልባትም ደዌው የእግዚአብሔርን ትዕዛዝ በመተላለፍ ያጋጠመው በሽታ በመሆኑ ዘመዶቹ በሙሉ ስለተውት ወይንም አናውቅህም ስላሉት እንዲሁም ዘመድ እያለው ነገር ግን ከእርሱ ስለራቁ ተስፋ በመቁረጥ ዘመድ የለኝም ሲል ተደመጠ፡፡ ዓለም እንዲህ ነው ሁሉም ነገር ሲኖርህ ሲሞላልህ ሰው የሚፈልገው ነገር ሁሉ ከአንተ ሲኖር ዘመደ ብዙ ትሆናለህ ሁሉም ሲያልቅ ግን ሁሉም ይቆማል፡፡
  2. በእግዚአብሔር አለመተማመን፡-  ብዙ ጊዜ ሰው የሚመካው በዘመዱ ወይንም በሀብቱ ሲሆን ይስተዋላል ነገር ግን ሁሉም ነገር ያልፋል፡፡ ሰው በዘመዱ ተስፋ አድርጎ ሁሉም ነገር አልሆን ሲል ወደ ማይሆን ሕይወት ውስጥ ሲገባ ይስተዋላል፡፡ ይህ ሁል ነገር የሚመጣው በእግዚአብሔር አለመተማመን የሚያመጣው ችግር ነው፡፡ትልቁ የሰው ልጆች እምነት በእግዚአብሔር ከሆነ ጥያቄያችን በሙሉ ወዲያውኑ መልስ ያገኝ ነበር፡፡ ቅዱስ ወንጌል እንዲህ ይላል፡- ዕብ.11፤5-7 ሄኖክ ሞትን እንዳያይ በእምነት ተወሰደ፥ እግዚአብሔርም ስለ ወሰደው አልተገኘም። ሳይወሰድ እግዚአብሔርን ደስ እንዳሰኘ ተመስክሮለታልና፤ ያለ እምነትም ደስ ማሰኘት አይቻልም፤ ወደ እግዚአብሔር የሚደርስ እግዚአብሔር እንዳለ ለሚፈልጉትም ዋጋ እንዲሰጥ ያምን ዘንድ ያስፈልገዋልና። ኖኅ ገና ስለማይታየው ነገር ተረድቶ እግዚአብሔርን እየፈራ ቤተሰቦቹን ለማዳን መርከብን በእምነት አዘጋጀ፥ በዚህም ዓለምን ኰነነ፥ በእምነትም የሚገኘውን ጽድቅ ወራሽ ሆነ። እግዚአብሔርን የምናስደስትበትና ለጥያቄያችን መልስ የምናገኘው በእምነት ነው፡፡ ቅዱሳን አባቶቻችን በአስቸጋሪ ሕይወት ውስጥ ያለፉት በእምነት ነው፡፡ እምነት ካለ መንገዳችን ሁሉ ቀና ይሆናል ለጥያቄያችን በቶሎ መልስ እናገኛለን፡፡ በአንጻሩም እምነት የሌለውና በሰው ወይንም በገንዘቡ የሚተማመን ሰው ከወደቀበትና እንዲሁም ከመጣበት የሕይወት ፈተና ውስጥ በቶሎ ሊነሳ አይችልም፡፡ መጻጉእ በአልጋ ላይ የተኛ 38 ዓመት ነው፡፡ ይህ ማለት ደግሞ መጻጉእ የታመመ ወይንም ደዌው የያዘው ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው ከመሆኑ በፊት ነው ማለት ነው፡፡ ምክንያቱም ጌታችን በዚህ ምድር የኖረው 33 ዓመት ነው፡፡ እንግዲህ ለሚያስተውል ሰው 38 ዓመት የተኛን ሰው በአንድ ቀን ተንሥና አልጋህን ተሸክመህ ሂድ ሲባል ምን ይሰማናል? ለእርሱ ሁሉም ይቻላል፡፡ ክቡራን እና ክቡራት ዛሬ ሰው ሁሉ ሳይታመም የታመመ ሆኗል ብቻውን ያወራል ከህሊናው ጋር ይታገላል፡፡ የሰው ሁሉ ሕይወት ፍጹም በእግዚአብሔር የመተማመኑ ነገር ደብዝዟል፡፡ መመካት በሚገባው አምላክ ደፍሮ እርሱ ይረዳኛል ሲል አይስተዋልም፡፡ ይልቁንም ሌላ ተጨማሪ ነገር አስቀምጦ በእግዚአብሔር እንደሚተማመን ብቻ በአንደበቱ ያወራል ውስጡ ግን የለም፡፡ ሁሉንም ነገር የሚያደርገው አማራጭን ይዞ ነው፡፡ ፀበል ለመፀበል ሲፈልግ ማን ይሻላል ብሎ ዕጣ አውጥቶ ነው፡፡ በአጠቃላይ እግዚአብሔር ያደርጋል የሚለው እምነት የጠፋ ይመስላል፡፡ ሰውን ተስፋ አድርጎ እንዲህ ሆንኩ ከማለት በእግዚአብሔር ተማምኖ የሚሰጠውን ነገር በተስፋ መጠባበቅ ይበልጣል፡፡ በእግዚአብሔር ፍጹም መተማመናችን የሚታወቀው የምንፈልገውን ነገር በትዕግሥት ደጅ ስንጸና ብቻ ነው፡፡ ሃይማኖት ያለው ሰው ትዕግሥት  ገንዘቡ ነች፡፡ ክርስቶስ ይህን ዓለም ሲያድን በትዕግሥት ውስጥ አልፎ ነው፡፡ በድለንም እንኳ በትዕግሥት ነው የተመለከተን፡፡ ዛሬም እንዲሁ፡፡ የሚገርመው ነገር ደግሞ ሰው አጥፍቶ እግዚአብሔር ዝም ሲለው አጥፍቼ ለምን ዝም አልከኝ አይልም በአንጻሩ ደግሞ ጥያቄ ጠይቆ እግዚአብሔር ሲታገስ ለምን ዝም አልክ ይላል፡፡ እግዚአብሔር አጥፍተን ለምን ዝም አለን? ስለማያቀውቅ ነው? ምክንያቱ እግዚአብሔር ሰው ከነ ኃጢአቱ እንዲጠፋ አይፈልግምና ነው፡፡ ጥያቄያችንም እንዲሁ ነው፡፡ እግዚአብሔር ትእግሥትኛ በመሆኑ ለጥያቄያችን መልስ እያለው ነገር ግን ከእኛ ትዕግሥትን ይፈልጋል፡፡ እርሱ ለሚሰጠው ነገር ጉድለት የለበትምና በትዕግሥት ሆነን ከጠየቅነው ሁሉኑም በጊዜው ያውም የሚጠቅመንን ያድርግልናል፡፡

ይቆየን ይቀጥላል