ዘወረደ
እንኳን ለታላቁ ጾም በሰላም አደረሳችሁ
በአጠቃላይ ዐቢይ ጾም ስምንት ሳምንታት ሲኖረው ከዚህም የመጀመሪያም ዘወረደ በመባል ይታወቃል ሁሉም ሳምንታት የራሳቸው የሆነ መጠሪያ አላቸው ሁሉንም በተራ እንመለከታቸዋለን ለዛሬው ግን የመጀመሪያውን ሳምንት እንመለከታለን፡፡
ዘወረደ
በመጋቤ ሐዲስ ፍቅረ ማርያም ባዘዘው
በቦሌ መንበረ ብርሃን ቅዱስ እግዚአብሔር አብ ቤተክርስቲያን የሐዲስ ኪዳን የትርጓሜ መምህር
ዘወረደ ሲባል እንግዲህ የግዕዝ ቃል ነው ወረደ ማለት ከላይ ወደታች መጣ ወይንም ወረደ ማለት ሲሆን ዘወረደ ሲል የመጣ ወይንም የወረደ ማለት ነው፡፡ እንገዲህ የመጀመሪያው የጾም ሳምንት ዘወረደ በማለት ይጀመራል ለምን ሲባል ከልዕልና ወደ ትሕትና ወይንም ከዙፋኑ ወደ ተዋረደው ሰው የመጣውን አምላክ የምናስብበት ዕለት ነው፡፡ ምክንያቱም እርሱ ሰው በመሆኑ ወይንም ከድንግል ማርያም በመወለዱ የወደቀውን ወይንም ክብር ያጣውን ሰው ወደ ክብሩ ይመለሰው ዘንድ ወዷልና፡፡ እርሱ ሰው ካልሆነ የሰው ልጆች መዳን አይፈጸምምና፡፡ ለዚህም ነው ዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 3፤11-15 ባለው ንባብ ውስጥ አካላዊ ቃል ወደዚህ ዓለም መምጣቱን ሲናገር እንዲህ ይላል ወአልቦ ዘዐርገ ውስተ ሰማይ ዘእንበለ ዘወረደ እምሰማይ ወልደ ሕጓለ እመሕያው፡፡ ወደሰማይ የወጣ የለም ወደ ሰማይ የወጣው ከሰማይ የወረደው የሰው ልጅ ክርስቶስ ነው በማለት ከድንግል ማርያም ነፍስና ሥጋን ተዋሕዶ ወደሰማይ ማረጉን ይገልጻል፡፡ ዘወረደ ማለት ይህ ነው፡፡ ከሰማይ የወረደ ወደ እኛ የመጣ እርሱ አካላዊ ቃል ነው፡፡ መዝ.39፤1 እግዚአብሔርን ደጅ ጸናሁት እርሱም ዘንበል አለልኝ ይላል፡፡ ይህ ማለት ከአዳም ጀምሮ የነበረው የሰው ልጅ በሙሉ እርሱ ሰው እንዲሆን በጾም በፀሎት የተማጸኑበት ልመና ወይን ፀሎት ነው ዘንበል አለልኝ ሲል ሰው ሆነልኝ ወደ እኔ መጣ የእኔን ደካማ አካል ነሣ ማለት ነው፡፡ እንግዲህ ዘወረደ ሲባል ይህ ነው ሰው ሰለሆነው አምላክ የምንማርበት ርእስ ነው፡፡
አምላክ ለምን ሰው ሆነ የወደቀውንና የጎሰቆለውን የሰው ልጅ ከዙፋኑ እንዳለ ለምን አያድነውም ነበር፡፡ ይህ ትልቅ ትምህርት የምንማርበት ርእስ ነው፡፡ በዘፍጥረት ምዕራፍ 3፤22 ላይ ሰው ስለመሆኑ አስቀድሞ ተነገሮ ነበር ያም ማለት እርሱ ሰው ሆኖ እኛን የእርሱ ልጆች አደረገን፡፡ ፍቅሩን አየን ቸርነቱን ቀመስን፡፡ እርሱ ዝቅ በማለቱ ሰማያዊው አምላክ ምድር መውረዱ እኛ ምን መሥራት እንዳለብን ተማርን፡፡ በተለይም የክርስትና ጉዞ ለሰው የምንኖርበት ሕይወት መሆኑን ተማርንበት፡፡ እርሱ ለጠፋው አንድ በግ ወደ እኛ መጣ ብዙ የባዘኑ፤ የሕወትን መንገድ የሳቱ፤ ከሕይወት ይልቅ ሞትን የመረጡ፤ በተሳሳተ መንገድ እየተጓዙ የእውነት መንገድ የሚመስላቸው፤ ከእግዚአብሔር ፈቃድ ይልቅ የራሳቸው የሀሳብ ፈቃድ ያሸነፋቸው ብዙ ሰዎች አሉ፡፡ እርሱ ለእኛ ሰው ከሆነ እኛ ለእኛነታችን ሕይወት ሕይወት መሆን እንዴት ተሳነን፡፡ እርሱ ከሰማይ ወረደ እኛ ግን ሁላችንም ከምድር ወይንም ከመሬት ተፈጥረን መሬቱ መሬትነቱን ናቀው፡፡ዘፍጥረት 2፤7 እግዚአብሔር አምላክ ሰውን ከምድር አፈር ሠራው ይላል፡፡ ሀቁና ውነታው ይህ ሆኖ እያለ መሬት መሬትን ሲንቀው ሁሉም ወደመሬት ሲመለሱ ማየት እንዴት ያማል፡፡ የሰው ማንነቱ የሚታወቅው ከእግዚአብሔር ጋር ሲኖር ብቻ ነው፡፡ እግዚአብሔር ያለው ሁሉም አለው እግዚአብሔር የሌለው ግን ሁሉም ነገር የለውም፡፡ ቢኖረውም ቅሉ በትካዜ የሚያልቅ ነው፡፡ ሰውን ማክበር ዝቅ ማለት እግዚአብሔርን ማየት ነው፡፡ እርሱ ለእኛ ዝቅ ብሏልና፡፡ በዚሁ ዕለት የሚሰበከው ምስብካም የሚያዘን ይህን ነው፡፡
‹‹ተቀነዩ ለእግዚአብሔር በፍርሃት
ወተሐሰዩ ሎቱ በረዓድ
አጽንዕዋ ለጥበብ ከመ ኢይትመዐዕ እግዚአብሔር››
ለእግዚአብሔር በፍርሃትና በመንቀጥቀጥ ደስ እያላችሁ ተገዙለት እግዚአብሔር እንዳይቆጣቸሁ ጥበብን አጽንታችሁ ያዟት፡፡ጥበብ ማለትም በጎ ምግባር፤ ፍቅር፤ትሕትና፤ የመሳሰሉት ናቸው፡፡ በአጠቃላይ እግዚአብሔር ያደረገልን በሙሉ ጥበብ ነው፡፡ እርሱም ጥበብ ይባላል፡፡ ዲዮስቆሮስ በቅዳሴው አይቴ ብሔራ ለጥበብ፡፡ የትበብ አገሯ ወዴት ነው በማለት ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ይናገራል፡፡በእርግጥ በንጹሕ ልብ በተሰበረ መንፈስ ውስጥ ያለ ሰው እርሱ የእግዚአብሔር ማደሪያ ሊሆን ይችላል፡፡ በአጠቃላይ ጥሩ ስብእና ባለው ሰውነት ውስጥ እግዚአብሔር ሥራን ይሰራል እመብርሃን ወላዲተ አምላክ የሆነቸው ከዓለም ተለይታ መገኘቷ ነው እኛ እኮ የእርሷ ልጆች ነን፡፡ እርሷም የእኛ እናት ናት መስቀል ሥር የተቀበልናት ልዑል እግዚአብሔር ሰው የሆነባት፤ ዓለምን ያዳነባት፡፡ ሁላችንም በሃይማኖት ጸንተን እንድንኖር ቸርነቱ ይርዳን አሜን
ይቆየን
